ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ 10ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በቅርቡ ያከብራል

የካቲት 25 /2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ''ለሰላም እንስራለን፣ በሰላም እንኖራለን፣ ዘረኝነትን እንጸየፋለን'' በሚል መሪ ቃል 10ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በቅርቡ እንደሚያከብር ገለጸ።

የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሃፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ ጉዳዩን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

ቀሲስ ታጋይ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ከመጪው እሑድ ጀምሮ የሚከበረው የምስረታ በዓል የጉባኤውን ያለፉ ዓመታት ስራዎች ጠንካራና ደካማ ጎኖች ይገመግማል።

በዚሁ መሰረት በዓሉ በፌዴራል ደረጃ በአዲስ አበባ የተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና የዲፕሎማቲክ ማሕበረሰብ አባላት በተገኙበት ይከበራል ነው ያሉት።

በክልል ደረጃ ደግሞ በጂማ ከተማ በፓናል ውይይትና በከተማዋ በሚገኘው ስታዲዬም 25 ሺህ ሰው በሚገኝበት ይከበራል ብለዋል ቀሲስ ታጋይ።

ቀሲስ ታጋይ ጂማ ከተማ የተመረጠበትም ምክንያት 1999 ዓ.ም ኃይማኖትን መሰረት ያደረገ ግጭት ባጋጠመበት ወቅት የአካባቢው የሃይማኖት በአባቶች በጋራ ሆነው ሁኔታውን ወደ ሰላም መቀየር መቻላቸውን ለማስታወስ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

በመሆኑም "ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በጂማ ዞን ኃይማኖትን ሽፋን ያደረገ ግጭት አልተከሰተም"  ብለዋል።

ቀሲስ ተጋይ አክለውም ጉባኤው ከተመሰረተ ጀምሮ በዜጎች መካከል ለዘመናት የቆየውን የሰላምና የአብሮነት እሴቶች የማጠናከር ስራ ሲሰራ መቆዩቱንም ገልጸዋል።

የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤው አልፎ አልፎ በአንዳንድ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶችንም በመፍታት ረገድ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አስታውሰዋል።

ጉባኤል በፖለቲከኞች መካከል የሚፈጠሩ ልዩነቶችን ለማጥበብና ለአገሪቱ ሰላም ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው ባይሳካም የኃይማኖት አባቶች መቀሌ በመሄድ ችግሮች በሰላምና በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ ጥረት ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በአገሪቱ ካሉ በሰላም ዙሪያ ከሚሰሩ ተቋማት መካከል ዋነኛው መሆኑን የገለጹት ቀሲስ ታጋይ ጉባኤው ይህንኑ ተግባር አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም