የኢንጅነሩ አሟሟት በአስቸኳይ ተጣርቶ ለህዝብ ይፋ እንዲሆን መንግስት ኃላፊነቱን ይወጣ-የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቱ - ኢዜአ አማርኛ
የኢንጅነሩ አሟሟት በአስቸኳይ ተጣርቶ ለህዝብ ይፋ እንዲሆን መንግስት ኃላፊነቱን ይወጣ-የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቱ
አዲስ አበባ ሃምሌ 20/11/2010 የኢንጅነር ስመኘው በቀለ አሟሟት በአስቸኳይ ተጣርቶ ለህዝብ ይፋ እንዲሆን መንግስት ኃላፊነቱን እንዲወጣ አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጠየቀ። ምክር ቤቱ በኢንጂነሩ ህልፈተ ህይወት የተሰማውን ሀዘን ገለጸ። የጋራ ምክር ቤቱ ለዛሬ የያዘውን አጀንዳ ለቀጣዩ ሳምንት ሐሙስ በማዘዋወር በታላቁ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ማናጀር ኢንጅነር ስመኘው በቀለ አሟሟት በፍጥነት ተጣርቶ ለህዝብ ይፋ በሚሆንበት ዙሪያ መግለጫ አውጥቷል። የኢንጂነሩ መሞት በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ ያነጣጠረ መሆኑን የገለጹት ፓርቲዎቹ ይህ ጉዳይ የኢንጅነር ስመኘው ሞት ብቻ ተደርጎ የሚወሰድ ሳይሆን በመቶ ሚሊዮን ህዝብ ላይ የተቃጣ መሆኑን ገልጸዋል። ኢንጅነር ስመኘው የበረሃውን ሐሩርና ቁር በመቋቋም የግድቡን ግንባታ ለማፋጠን በትጋት ከመሥራታቸው ባሻገር ኢትዮጵያውያን እውቀታቸውን ወደ ተግባር በመለወጥ በኩል ብዙ ባለሙያዎችን ያፈሩ የኢትዮጵያውያን ባለውለታ መሆናቸውን አስታውቋል። የጋራ ምክር ቤቱ የኢንጅነሩ አሟሟት በአስቸኳይ ተጣርቶ ለህዝብ ይፋ እንዲሆን መንግስት የፈጠነ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርቧል። ለወደፊቱም መሰል ወንጀሎች እንዳይፈጸሙ በህዝብ ውስጥ ተደብቀው ፀረ-ህዝብ ዓላማ የሚያራምዱ ኃይሎችን መንግስት ያለውን የፀጥታና የደህንነት መዋቅሩን በመጠቀም ግዴታውን ሊወጣ ይገባልም ብሏል። እንደ ኢንጅነር ስመኘው ያሉ በአገሪቷ የልማት ሥራ ላይ ትልቅ ሚና በመጫወት ላይ የሚገኙ የልማት አርበኞችም መንግስት ልዩ ጥበቃ ሊያደርግላቸው እንደሚገባም ምክር ቤቱ አሳስቧል። ለዚህም ባለፈው ሰኔ 16 በመስቀል አደባባይ የተፈፀመውን የቦንብ ፍንዳታ ፈፃሚዎቹን መንግስት በአስቸኳይ አጣርቶ በህግ ተጠያቂ በማድረግና ጉዳዩን ይፋ የማድረግ ሁኔታ በመዘግየቱ ለወንጀል ፈፃሚዎች አመቺ ሁኔታ እየፈጠረ መሆኑንም ምክር ቤቱ ገልጿል። ህብረተሰቡም ከስሜታዊነት ወጥቶ ከመንግስት ጎን በመቆም ለሠላም መስፈን የድርሻውን መወጣት እንዳለበት የገለጸው የጋራ ምክር ቤቱ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩ አላስፈላጊ ግጭቶች የፀጥታ ኃይሎች ወንጀለኞችን ለመያዝ የሚያከናውኑትን ሥራ የሚያስተጓጉል በመሆኑ በዚህ ተግባር ላይ የተሰማሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስቧል። መንግሥት የኢንጅነር ስመኘው በቀለ ሞትን ምክንያት በማድረግ በአገሪቷ ብሄራዊ የሐዘን ቀን እንዲያውጅና የልማት አርበኛ መሆናቸውን የሚገልጽ ሐውልት እንዲያቆምላቸው የጋራ ምክር ቤቱ ጠይቋል። የጋራ ምክር ቤቱ ለኢንጅነር ስመኘው በቀለ ቤተሰቦች፣ ወዳጆች፣ የሥራ ባልደረቦችና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መፅናናትን ተመኝቷል። አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቱ 13 ፓርቲዎችን ያቀፈ ነው።