ስድስተኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ በትብብር እየሰሩ መሆናቸውን ፓርቲዎች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ስድስተኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ በትብብር እየሰሩ መሆናቸውን ፓርቲዎች ገለጹ
ጋምቤላ፤ የካቲት 25/2013(ኢዜአ) ስድስተኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና በህዝብ ዘንድ ታአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በትብብር እየሰሩ መሆናቸውን በጋምቤላ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ገለጹ።
ምርጫው ያለአንዳች እንከን እንዲሳካ ሰላማዊና ዴሞክራሲዊ ፉክክር ለማድረግ እየተዘጋጁ መሆናቸውን አመራሮቹ ለኢዜአ ተናግረዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ጋምቤላ ክልል ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ላክድር ላክባክ እንዳሉት ፤ ብልጽግና በክልሉ ከሚገኙት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ካለፈው ዓመት ጀምሮ በትብብር እየሰራ ይገኛል።
አሁን ላይም ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ፣ በህዝብ ዘንድ ታአማኒና ተቀባይነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅም በመስራት ላይ እንዳሉ ገልጸዋል።
መጪው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ ፍጹም ታማኒነት ያለው ሆኖ ፍፃሜውን እንዲያገኝ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በትኩረት እየሰሩ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የጋምቤላ ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ / ጋህነን/ ጸሐፊ አቶ ተዘራ ኃለማሪያም ናቸው።
በተወሰኑ ወረዳዎች ከግንዛቤ ማነስ ከሚታዩ ጥቃቅን ችግሮች በስተቀር በክልሉ እስካሁን ያለው ሂደት መልካም እንደሆነ ገልጸዋል።
በቀጣይም ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ፓርቲዎችም ሆኑ መላው የክልሉ ህዝብ ከመንግስት ጎን በመሆኑን ሊሰሩ እንደሚገባ አቶ ተዘራ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ኢዜማ/ የጋምቤላ ቅርንጫፍ ምክትል መሪ ኮማንደር ጋድቤል ቦል በበኩላቸው ስድስተኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ ሰላማዊና ፍትሃዊ እንዲሆን ኢዜማ በክልል ከሚገኙ ሌሎች ፓርቲዎች ጋር እየሰራ ነው ብለዋል።
ለምርጫው ሰላማዊነትና ፍትሃዊነትም የክልሉ ህዝብ የድርሻውን እንዲወጣም መልክታቸውን አስተላልፈዋል።
ብልጽግናን ጨምሮ በጋምቤላ ክልል ስድስት የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው እንደሚፎካከሩ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተገኘው መረጃ ያመለከታል።