በመተከል ዞን የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተናን በስኬት ለማጠናቀቅ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በመተከል ዞን የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተናን በስኬት ለማጠናቀቅ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል
የካቲት 24/2013 (ኢዜአ) በመተከል ዞን የ12 ክፍል አገር አቀፍ ፈተና በስኬት እንዲጠናቀቅ አስፈላጊ ቅድመ ዝግጀት መድረጉን በዞኑ የተቋቋመው የተቀናጀ ግብረ ሃይል ገለጸ።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና አስመልክቶ ለፈተና ጣቢያ ኃላፊዎች ገለጻ ተደርጓል።
የመተከል ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መልካሙ በሻ ለፈተና ጣቢያ ኃላፊዎች አስቀድሞ ገለጻ እየተደረገ ያለው ፈተናው ያለምንም የፀጥታ ችግር ህግና ስርዓትን ተከትሎ እንዲሰጥ ለማድረግ ታስቦ መሆኑን ተናግረዋል።
ፈተናው በስኬት እንዲጠናቀቅ ከመተከል ዞን የተቀናጀ ግብረ ኃይል ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
በመተከል ዞን አገር አቀፍ ፈተናው በ12 የመፈተኛ ጣቢያዎች እንዲሚሰጥም ነው አቶ መልካሙ ያመለከቱት።
የምዕራብ ዕዝ ምክትል አዛዥና የመተከል ዞን የተቀናጀ ግብረ ኃይል አባል ብርጋዴር ጄኔራል አለማየሁ ወልዴ ፈተናው ያለችግር ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ በቅንጅት አስፈላጊው ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ገልጸዋል።
የፈተና ጣቢያ ኃላፊዎች ፈተናው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡም አስገንዝበዋል።
በፈተና አሰጣጥ ወቅት ችግሮች የሚፈጠሩ ከሆነ በአካባቢው ካለ የፀጥታ አካል ጋር በመቀናጀት በኃላፊነት ተንቀሳቅሶ መፍትሄ ማበጀት አስፈላጊ መሆኑንም በአጽንኦት ተናግረዋል።
የ2012 ዓ.ም አገር አቀፍ ፈተና ከየካቲት 29 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚሰጥ መገለጹ ይታወሳል።