ሴቶች በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአመራርነትና ውሳኔ ሰጪነት ያላቸው ድርሻ ዝቅተኛ ነው-- ጥናት - ኢዜአ አማርኛ
ሴቶች በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአመራርነትና ውሳኔ ሰጪነት ያላቸው ድርሻ ዝቅተኛ ነው-- ጥናት
የካቲት 24/2013 (ኢዜአ) ሴቶች በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ በአመራርነትና ውሳኔ ሰጪነት ቦታ ላይ ያላቸው ድርሻ ዝቅተኛ መሆኑን አንድ ጥናት አመለከተ።
በኢትዮጵያ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ውሳኔ ሰጪነትና አመራርነትን በሚመለከት አውደ ጥናት ተካሂዷል።
ጥናቱ በአገሪቱ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሥርዓተ ጾታ አካታችነት ላይ አተኮሮ የተካሄደ መሆኑ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስርዓተ ጾታ እኩልነትና ሴቶችን የማብቃት ክፍል (ዩ.ኤን.ዉሜን) ጋር በመተባበር የተካሄደ ነው።
የጥናት ግኝቱ ላይ ከሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር እና ከተለያዩ ሲቪክ ማህበራት ተወካዮች ጋር ዛሬ ውይይት ተካሂዷል።
በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የስርዓተ ጾታ እና አካታችነት ማናጀር ወይዘሮ መድሀኒት ለገሰ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ጥናቱ በኢትዮጵያ ውስጥ ተመዝግበው በሚንቀሳቀሱ 70 የሚሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ የተካሄደ ነው።
ጥናቱ ከተካሄደባቸው ፓርቲዎች በ21ዱ ውስጥ ብቻ ሴቶች በማዕከላዊ ኮሚቴ፣ በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፣ በኦዲት ኮሚቴና በመሳሰሉት ውስጥ በአባልነት ተወክለዋል።
ሴቶች በአመራርነት እና በውሳኔ ሰጪነት ቦታ ላይ የተቀመጡት በአምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ብቻ መሆኑንም ጥናቱ አመላክቷል።
ይህም ሴቶች በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ በውሳኔ ሰጪነትና አመራርነት ቦታ ላይ ያላቸው ድርሻ ዝቅተኛ መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነ ጥናቱ ማመላከቱን ነው ወይዘሮ መድሀኒት የገለጹት።
ለዚህም በተለይ ለሴቶች ምቹ ያልሆኑ የፓርቲ የውስጥ መዋቅሮች መኖር፣ ኃይልና ጥቃትን መሰረት ያደረገ የፖለቲካ ባህል እና ምህዳር መኖር በምክንያትነት ተጠቅሰዋል።
በተጨማሪም የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ የማይዘግቡ ከዘገቡም አሉታዊ እና አፍራሽ ጎኑን ብቻ የሚሸፍኑ መገናኛ ብዙሃን መስፋፋት መንስኤዎች መሆናቸው ነው በጥናቱ የተመላከተው።
በመሆኑም የፖለቲካ ፓርቲዎች የስርዓተ ጾታ እኩልነት መዋቅሮችና አጀንዳዎችን በፓርቲ ፕሮግራሞች ውስጥ በማካተት የሴቶች ውክልና ከአባል እስከ አመራር እንዲጨምር ጥረት ማድረግ እንደሚገባቸው በጥናቱ ተገልጿል።
በዚህ ረገድ ያለውን ክፍተት ለመሙላትም የማህበረሰብ አንቂዎች፣ የሴቶች መብት ተሟጋቾች እና የሲቪል ማህበረሰቡ ሚና ከፍተኛ እንደሆነም ነው የተገለጸው።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን በማሻሻልና ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ ማጎልበት እንደሚገባ አንስተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ለሴቶች በትምህርት እና በስልጠና ተገቢ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ የሴት ማህበራት እንዲጠናከሩ የማድረግ ሥራ መሰራት እንዳለበት ነው ያመለከቱት።
ሴቶች ራሳቸው በፖለቲካው መስክ ላይ ተሳትፎ ለማድረግ ያላቸውን የተዛባ አመለካከት ማሻሻልና መቀየር እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።
የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሙና አህመድ፣ የዘንድሮውን የዓለም የሴቶች ቀን ምክንያት በማድረግ በሴቶች እኩልነት ዙሪያ የአንድ ወር መርሃ ግብር መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።
በእዚህም በተለይ በሴቶች አመራርነትና ውሳኔ ሰጪነት ሚና፣ ታዳጊ ሴቶችና ትምህርት፣ ሴቶችን በኢኮኖሚ ማብቃት እንዲሁም ጾታዊ ጥቃትን መከላከል በሚሉ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ንቅናቄ እንደሚካሄድ ገልጸዋል።
ይህን ተከትሎም መዋቅራዊ ችግሮችን መፍታት፣ የሴቶችን ፖሊሲ መፈተሽ እና መከለስ እንዲሁም ሌሎች የህግ ማዕቀፎችን ማየት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ሰፊ ሥራዎችን ለመስራት ጥረት ይደረጋል ብለዋል።