ቀጥታ፡

የእሳት ቃጠሎ ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ማውደሙን ፖሊስ አሰታወቀ

ነገሌ፤ የካቲት 24/2013( ኢዜአ) በጉጂ ዞን ሻኪሶ ወረዳ "መጋዶ " የገጠር ከተማ በደረሰው የእሳት ቃጠሎ ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ማውደሙን ፖሊስ አስታወቀ።

በቀበሌው ትናንት ቀን ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ የደረሰው የእሳት ቃጠሎ በሰው ህይወት ላይ ያደረሰው ጉዳት እንደሌለ ተመልክቷል።

የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ወንጀል ምርመራ ክፍል ሀላፊ ዋና ሳጂን ታጂዎ ቱርፋ እንደገለጹት በእሳት ቃጠሎው  21 የንግድ እና ስድስት  የመኖሪያ ቤቶች ከጥቅም ውጭ ሆነዋል፡፡

በግለሰቦቹ መኖሪያ ቤት ውስጥ ተከማችቶ የነበረ ጤፍ፣ ስንዴና በቆሎ በቃጠሎው ሙሉ በሙሉ መውደሙን አመልክተዋል፡፡

የእሳት ቃጠሎው የከፋ ጉዳት ሳያደርስ በጸጥታ ሃይልና የአካባቢው ማህበረሰብ ርብርብ መቆጣጠር መቻሉን የገለጹት ዋና ሳጂን ታጂዎ ፤ በአደጋው   6 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር የሚገመት የ20 አባወራዎች ንብረት  ጉዳት ደርሶበታል ብለዋል፡፡

የእሳት አደጋው መንስኤ እየተጣራ ቢሆንም  ከኤሌክትሪክ መስመር  መገናኘት ጋር ተያይዞ ሊሆን እንደሚችል ጥርጣሬ እንዳለ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም