የፖለቲካ ፓርቲዎች የእጩዎች ምዝገባ ጊዜ እንዲራዘምላቸው ጠየቁ - ኢዜአ አማርኛ
የፖለቲካ ፓርቲዎች የእጩዎች ምዝገባ ጊዜ እንዲራዘምላቸው ጠየቁ
የካቲት 24 ቀን 2013 (ኢዜአ) የፖለቲካ ፓርቲዎች የእጩዎች ምዝገባ ጊዜ እንዲራዘምላቸው ሲጠይቁ፤ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ ምዝገባው እንደማይራዘም ገልጾ ፓርቲዎቹ ያለውን ጊዜ በአግባቡ እንዲጠቀሙበት አሳስቧል።
6ኛውን አገራዊ ምርጫ በማስመልከት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የእጩዎች ምዝገባ ያለበት ሁኔታ፣ የቦርዱ የመረጃ ማዕከል አሰራርና በቀጣይ የሚከናወኑ ተግባራት ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል።
ቦርዱ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የእጩዎች ምዝገባ ጊዜ ከየካቲት 8 እስከ 21 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ የሚካሄድ የነበረ ሲሆን ቦርዱ የእጩዎች ምዝገባ ሂደት በተገመገመበት ወቅት የምርጫ ክልል ቢሮዎች ለመከፈት በመዘግየታቸውና በሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች የእጩዎች ምዝገባ እስከ የካቲት 25 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ እንዲራዘም ማድረጉ ይታወሳል።
የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ዛሬ በተካሄደው መድረክ አሁንም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በተለያዩ ምክንያቶች የእጩዎች ምዝገባ ያልጀመሩ እንዳሉ አመልክተዋል።
በመሆኑም አሁንም የተጨመረው ቀን የሚያንስ በመሆኑ እንደ አስፈላጊነቱ ታይቶ የእጩዎች ምዝገባ ጊዜ በድጋሚ እንዲራዘም ጠይቀዋል።
የተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከእጩዎች ምዝገባና ከአጠቃላይ የምርጫ ሂደት ጋር በተያያዘ በእጩዎቻቸውና አባላቶቻቸው ላይ ማወከብ እያጋጠመ እንደሆነ ተናግረው፤ በታችኛው መንግስታዊ መዋቅር ውስጥ የሚገኙ የገዥው ፓርቲ አባላት ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲይዙ መደረግ እንዳለበት ገልጸዋል።
በብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት የምርጫ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዛዲግ አብረሃ ፓርቲያቸው ነጻ፣ ገለልተኛና ፍትሃዊ ምርጫ እንዲካሄድ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ፓርቲው አባላቶቹ የሚመሩበት የስነ-ምግባር መመሪያ ማዘጋጀቱን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በበኩላቸው በአብዛኛው የአገሪቱ አካባቢዎች የእጩዎች ምዝገባ እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው፤ "ቦርዱ የእጩዎች ምዝገባ ያልጀመሩ አካባቢዎች ፈጥነው እንዲገቡ ያደርጋል" ብለዋል።
የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና እጩዎች ላይ የሚደርስ እንግልትና ማዋከብ ካለም ፈጥነው ለቦርዱ እንዲያሳውቁና የእርምት እርምጃም እንደሚወሰድ ገልጸዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች እጩዎችን ለማስመዝገብ ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ አሳስበዋል።