የጆሮ ሕመም ሲሰማ ፈጥኖ በመታከም ሊከሰት የሚችለውን የከፋ ችግር መከላከል ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የጆሮ ሕመም ሲሰማ ፈጥኖ በመታከም ሊከሰት የሚችለውን የከፋ ችግር መከላከል ይገባል

የካቲት 24/2013 (ኢዜአ) በጆሮ ላይ ሕመም ሲሰማ ወደ ሕክምና ተቋም ፈጥኖ በመሄድ በጆሮና በመስማት ላይ ሊከሰት የሚችለውን የከፋ ችግር መከላከል እንደሚገባ ተገለጸ።
የዓለም የመስማት ቀን "የመስማት ሕክምና ለሁሉም" በሚል መሪ ሀሳብ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም የሕክምና ኮሌጅ እና በክርስቲያን ብላይንድ ሚሽን ትብብር ዛሬ ተከብሯል።
በተያዘው ዓመት የዓለም ጤና ድርጅት ይፋ ያደረገው መረጃ በዓለም ላይ ከአምስት ሰዎች አንዱ የመስማት ችግር እንዳለበት ያመላክታል።
የጆሮ ህመም ሲያጋጥም በአፋጣኝ ሕክምና ማግኘት ካልተቻለ ለመስማት መሳንና ለሌሎች ተያያዥ የጤና ችግሮች ሊያጋልጥ ይችላል።
የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅን የወከሉት ዶክተር ሲሳይ ጽጌ እንዳሉት ሁሉም ሰው በጆሮና በመስማት ላይ ሊከሰቱ ከሚችሉ ችግሮች አስቀድሞ መጠንቀቅ ይኖርበታል።
የመስማት ችግር ከሚፈጥሩ ምክንያቶች መካከል ከፍተኛ ድምፅ፣ ሲጃራ ማጤስ፣ በዘር መተላለፍ፣ ያለአግባብ የሚወሰድ መድኃኒት፣ ተዋህሲያን እና ሌሎች የጥንቃቄ ጉድለቶችን ጠቅሰዋል።
ዶክተር ሲሳይ እንዳሉት ችግሩን ለመከላከል ማንም ሰው በጆሮው ላይ ሕመም ሲሰማው ፈጥኖ ወደ ሕክምና ተቋም መሄድ ይኖርበታል።
"ጆሮን ከሚጎዱ ነገሮች ከመጠንቀቅ ባለፈ በተለይ ሴቶች በእርግዝና ወቅት ተመጣጣኝ ምግብ መመገብ ይኖርባቸዋል" ብለዋል።
የጆሮና የመስማት ችግሮች ሕክምና በጤና ተቋማት በስፋት እንዲሰጡ ለማድርግ ከክርስቲያን ብላይንድ ሚሽን ጋር ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ደክተር ሲሳይ ጠቁመዋል።
ከኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማ`በር ጋር በመተባበርም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል።
በክርስቲያን ብላይንድ ሚሽን የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሚስተር ፍራንሲስኮ ጉሌቲ በበኩላቸው "በጆሮና በመስማት ላይ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በስፋት መስራት ያስፈልጋል" ብለዋል።
ድርጅታቸው የተለያዩ የግንዛቤ መፍጠሪያዎች እየሰራ መሆኑንና ለአራት የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅ ሐኪሞች የአንድ ዓመት ስልጠና በኦንላይን እየሰጠ መሆኑን ገልፀዋል።
በተጨማሪም በመገናኛ ብዙሃን ስለ ጉዳዩ የግንዛቤ ትምህርቶችን እያሰራጨን ነው ብለዋል።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት መንግስት፣ ፖሊሲ አውጪዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በጋራ መስራት እንዳለባቸው ነው ዳይሬክተሩ ያመለከቱት።