በጋምቤላ ክልል መጪው ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ዝግጅት ማድረጉን ፖሊስ አስታወቀ

57

ጋምቤላ ፤ የካቲት 24/2013 (ኢዜአ)  ስድስተኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ በጋምቤላ ክልል ፍጹም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን ፖሊስ አስታወቀ።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አቡላ ኡቦንግ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ምርጫው ያላንዳች ችግር በሰላም እንዲጠናቀቅ   ፖሊስ ከክልል እስከ ወረዳ አደረጃጀት በመፍጠር እንዲጠናከር ተደርጓል።

በዚህም የምርጫ ቦርድ ያወጣውን የጊዜ ሰሌዳ መሰረት በማድረግ ፖሊስ ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ በገለልተኝነት ኃላፊነቱን እንዲወጣ በሚያስችል መልኩ መሰናዳቱን አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅት በክልሉ በሚገኙ 14 ምርጫ ክልሎች በእያንዳንዱ ሶስት  ንዑሳን ኮሚቴ ያሉት የፖሊስ መዋቅር በማደራጀት ምርጫውን ሰላማዊና ፍትሃዊ ሆኖ በስኬት እንዲጠናቀቅ ዝግጅቱ መጠናቀቁን  ገልጸዋል።

በምርጫ ክልሎች በተደራጁት የፖሊስ መዋቅሮችም በበቂ ተሽከርካሪና የሰው ኃይል የማሟላት ተግባር በማከናወን  ስምሪቶች መጀመራቸውን  ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።

በተጨማሪ ኮሚሽኑ ከፌደራል ፖሊስ ጋር በመቀናጀት ምርጫው ያላንዳች ችግር እንዲሳካ  ኮሚቴ በማዋቀር እየሰራ መሆኑንም  አስረድተዋል።

ምርጫው ሰላማዊ በመሆነ መልኩ እንዲጠናቀቅ ፖሊስ ለሚያከናውናቸው ስራዎች መሳካት ህብረተሰቡ በመደገፍ የበኩሉን ሚና እንዲወጣም ኮሚሽነር  አቡላ  ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም