ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጋር ይወያያሉ

አዲስ አበባ ሀምሌ 20/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ማይክ ፔንስ ጋር ሊወያዩ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሜሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን ጋር ለመወያየት ትናንት አሜሪካ መግባታቸው ይታወቃል። ዶክተር አብይ ከአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ማይክ ፔንስ ጋር በሁለቱ አገሮች ግንኙነት እንዲሁም በአካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ ይወያያሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል። ከዚህም በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከት ከሚያራምዱ ኢትዮጵያዊያን የፓርቲ መሪዎች ጋር እንደሚነጋገሩም ታውቋል። በትናንትናው ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአሜሪካ የኃይማኖት አባቶች የእርቀ-ሰላም መድረክ ማጠናቀቂያ ላይ በመገኘት ንግግር ማድረጋቸው ይታወሳል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ትናንት በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዲፕሎማቶች እና በአካባቢው በሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ዶክተር አብይ በሰሜን አሜሪካ እያደረጉ ያሉት ጉብኝት እንዲሳካ የኤምባሲው ሰራተኞች እና ኢትዮጵያዊያኑ ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል። በንግግራቸውም በአገሪቱ ያሉት ኢትዮጵያዊያን ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው "እናንተን ግማሽ አካላችንን ትተን ወደፊት መሄድ አንችልም" ብለዋል። በጋራ የአገራችንን ሰላምና ልማት እናረጋግጣለን ሲሉም ገልጸዋል። "ነጻነትን ያረጋገጠ ህዝብ ሰላም፣ ዴሞክራሲ እና ልማትን ማረጋገጥ አያቅተውም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መጪው ጊዜ ብሩህ ነው፤ እጅ ለእጅ ተያይዘን እንስራ" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሜሪካ በሚኖራቸው ቆይታ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው እየተካሄደ ላለው ሁለንተናዊ ለውጥ አካል በመሆን ለአገሪቱ ልማትና ዕድገት አስተዋጽኦ ማበርከት በሚችሉበት ሁኔታ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም