የድል በዓሉ ኢትዮጵያዊያን ያደረጉት አኩሪ ተጋድሎ የሚዘከርበት በመሆኑ ወጣቱ ሊያስቀጥለው ይገባል -አቶ አገኘሁ ተሻገር

ባህርዳር ፤የካቲት 23/2013(ኢዜአ) የአድዋ ድል በዓል ከሀገራችን አልፎ የመላው አፍሪካዊያን ነጻ መውጣት ኢትዮጵያውያን ያደረጉት አኩሪ ተጋድሎ የሚዘከርበት በመሆኑ ወጣቱ ሊያስቀጥለው ይገባል ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር ተናገሩ።

125ኛው የአድዋ ድል በዓል በክልሉ ደረጃ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንደተናገሩት በዓሉ የኢትዮጵያ ህዝቦች ለነጻነታቸው የከፈሉት መስዋዕትና የተገኘው ድል የሚዘከርበት ነው።

አውሮፓውያን የኢትዮጵያን  ክብር ለማዋረድና ህዝቡን ለመጨቆን  ቢጥሩም ጀግኖች አባቶች በጽናት ታግለው ባስመዘገቡት ድል ወደ ዲፕሎማሲያዊ ድርድር እንዲመጡ ያስገደደ አኩሪ ገድል መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም  ኢትዮጵያ በአፍሪካ ደረጃ የተቀነቀነው የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ መሪ ተዋናይ ለመሆን መብቃቷን አውስተዋል።

የዘንድሮው የዓድዋ በዓል እየተከበረ ያለው የኢትዮጵያ ህዝቦች በተለይም የአማራ ህዝብ የምንጊዜም ጠላት የሆነው የህውሃት ጁንታ በተቀበረበት ማግስት በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።

የአድዋ ድልና የህግ ማስከበር ዘመቻው የሚያመሳስላቸው የኢትዮጵያ ጠላቶች በእብሪትና ዘመናዊ የጦር መሳሪያ እስከፍንጫው መታጠቅ ማሸነፍ የማይቻል መሆኑን የተረጋገጠበት የታረክ ክስተት መሆኑንም  ጠቅሰዋል።

"አባቶቻችን በእውነት ላይ ተመስርተው ለነጻነታቸው መታገላቸውን አስታውሰው የአድዋ ድል በዓል  ከሀገራችን  አልፎ የመላው አፍሪካዊያን ነጻ መውጣት ኢትዮጵያዊያን ያደረጉት አኩሪ ተጋድሎ የሚዘከርበት በመሆኑ ወጣቱ ትውልድ ሊያስቀጥለው ይገባል ብለዋል።

የአማራ ክልል የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት  አቶ ዳኝነት አያሌው  በበኩላቸው የአድዋ ድል በዓል በመንግስት ደረጃ የላቀ እውቅና ተሰጥቶ መከበሩ የአርበኞችን ገድል የዘከረ መሆኑን ገልጸዋል።

ጀግኖች አባቶች የጣሊያንን ወራሪን በአድዋ በማሸነፍ ያስረከቡንን የተከበረች ሀገር አሁን ላይ ተማርን የሚሉ ጥቂት ወገኖች ሊያጠፏት ሲሯሯጡ መታየቱ የሚያሳዝን ነው ብለዋል።

የዚህ መሰረት የሆነው ዘርን መሰረት ያደረገ የፖለቲካ አደረጃጀት ወገን ከወገን የሚለያይና ሀገርን የሚያፈርስ በመሆኑ ወጣቱ ትውልድ አጥብቆ ሊዋጋው  ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

"አባቶቻችን በደም የተጻፈ ታሪክ፣ በአጥንታቸው የታጠረ ዳር ድንበርና ሉአላዊነቷ የተከበረ ሃገር አስረክበውናል" ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሙሉቀን አዳነ ናቸው።

ጀግኖች አባቶች በአድዋ በከፈሉት መስዋዕትነት ያስገኙት ድል ለዓለም ጥቁር ህዝቦችና በቅኝ ግዛት ለወደቁ ፍትህ፣ ነጻነትና ርትዕ ያስገኘ በመሆኑ በዓሉ በዓለም ላይ ሲዘከር የሚኖር መሆኑን አስረድተዋል።

የአሁኑ ትውልድም የአባቶቹን ታሪክ በአግባቡ በመረዳት ለሚካሄደው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የበኩሉን እንዲወጣ አሳስበዋል።

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ  ዶክተር ድረስ ሳህሉ በበኩላቸው የአድዋ በዓል ጀግኖች አባቶች በአንድነት በመሰለፍ ከአእምሮ የማይጠፋ ጉልህ ታሪክ የፈጸሙበት አኩሪ ገድል መሆኑን ተናግረዋል።

የአሁኑ ትውልድም አባቶቻችን በከፍታ ማማ ላይ ያስረከቡንን ኢትዮጵያን ወደ ላቀ ከፍታ በመውሰድ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት መወጣት አለበት ብለዋል።

የአድዋ በዓል በአማራ ክልል በየደረጃው በፓናል ውይይት፣ እግር ጉዞ፣ ኪነ ጥበብና ሌሎች ዝግጅቶች ሲከበር ሰንብቶ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት ዛሬ የማጠናቀቂያ ሥነ-ሥርዓት ተከናውኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም