የአባቶቻችንና እናቶቻችን ታላቅ ገድል ወራሾችና አድናቂዎች ብቻ ሳንሆን የእኛን ትውልድ ታሪክ በማይደበዝዝ ቀለም መጻፍ አለብን ... ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
የአባቶቻችንና እናቶቻችን ታላቅ ገድል ወራሾችና አድናቂዎች ብቻ ሳንሆን የእኛን ትውልድ ታሪክ በማይደበዝዝ ቀለም መጻፍ አለብን ... ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 23/ 2013 (ኢዜአ) “የአባቶቻችንና እናቶቻችን ታላቅ ገድል ወራሾችና አድናቂዎች ብቻ ሳንሆን የእኛን ትውልድ ታሪክ በማይደበዝዝ ቀለም መጻፍ አለብን” ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
125ኛው የዓድዋ የድል በዓል በአዲስ አበባ በዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።
በበዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአዲስ አ በባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እንደገለጹት፤ አድዋን ስናስብ ከድል ብስራቱ በላይ የመቻል መንፈሱ ይገዝፋል።
“የአድዋ ድል ወሰን ‘አይቻልምን’ መስበር ነው” ያሉት ምክትል ከንቲባዋ፤ “አድዋ አባቶቻችንና እናቶቻችን መከፋፈልና ግለኝነትን ትተው ተከባብረውና ተፈቃቅረው እንደሰርገኛ ጤፍ ህብር ፈጥረው፤ በህብር ማሸነፍን ጥበብ ተላብሰው በአድዋ ያረጋገጡት የአይበገሬነት ክብረ ወሰን ማሳያ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
“ከአድዋ ድል መማር ያለብን መተኪያ የሌላትን ውድ አገራችንን አንድ ሆነን ማስከበርና ማሻገርን ነው” ያሉት ወይዘሮ አዳነች፤ “ይህም ውስጣዊ አንድነታችንን አጠናክረን በጋራ ጠላት ላይ በጋራ በመዝመት የጋራ አገር መገንባትን ይጠይቃል” ብለዋል።
የጋራ ጠላት የሆነውን ጥላቻ፣ ቂም፣ በቀል፣ መናናቅ፣ መጠላለፍ፣ የፖለቲካ ቁማርን፣ ጠቅላይነትና አግላይነት፣ አለመተሳሰብ፣ አሉባልታውን በመተው የመፍትሄው አካል መሆን እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
ይህንን ተግዳሮት የበዛበትን ጊዜ በጋራ ለማለፍ ከዳር እስከዳር እጅ ለእጅ በመያያዝ ለማለፍ በአንድነት መቆም እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
“የአባቶቻችንና እናቶቻችን ታላቅ ገድል ወራሾችና አድናቂዎች ብቻ ሳንሆን ወይም በታሪክ ከምንጣላ የዛሬውን ጠላት ድህንትንና ድንቁርና በማሸነፍ የበለጸገች አገርና ትውልድ ለማውረስ ታሪካዊ ሃላፊነታችንን በመወጣት የእኛን ትውልድ ታሪክ በማይደበዝዝ ቀለም መጻፍ አለብን” ብለዋል።
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን በበኩላቸው፤ ትውልዱ ከአጼ ሚኒሊክ ዘመቻ ህብረት በመማር ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከጫፍ እንዲደርስ መስራት እንደሚገባ መክረዋል።