ቀጥታ፡

የአደዋ መታሰቢያ በዓል በአጼ-ሚኒሊክ የትውልድ ስፍራ በድምቀት ተከበረ

ደብረብርሀን ፤ የካቲት 22/ 2013(ኢዜአ) 125ኛው ዓመት የአድዋ መታሰቢያ በዓል በአጼ -ሚኒሊክ የትውልድ ስፍራ በሰሜን ሸዋ ባሶና ወራና ወረዳ ዛሬ በድምቀት ተከበረ፡፡

በደብረብርሀን ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት በዓሉ በስፍራው የተከበረው "አድዋ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ብርሀን ነው" በሚል መሪ ሀሳብ ነው።

በበዓሉ አከባበር ሥነ-ሥርዓት በዩኒቨርስቲው የማህበራዊ ሳይንስና ሥነ-ሰብ ኮለጅ ዲን ዶክተር ገብሬ ታፈረ እንዳሉት ወጣቶች የሀሰት ትርክቶችን በማረም በሀገረ መንግስት ግንባታ የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት መወጣት አለባቸው።

ለዚህም ለመላው የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ምልክት የሆነውን የአድዋ ድል በአግባቡ በመመርመር፣ ምክንያታዊ አስተሳሰብና አመለካከትን መያዝ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲውም በታሪክ የትምህርት ክፍሉ አማካኝነት ወጣቱ ትውልድ በጥናት ላይ የተመሰረተ እውቀትና ክህሎት ለማስጨበጥ የድርሻውን እንደሚወጣ ገልጸዋል።

በዞኑ የሚገኙ ታሪካዊ ቦታዎችን ለወጣት ተመራማሪዎች በማስተዋወቅና ፋይዳቸውን በማስገንዘብ በአድዋ ድል የተገኘውን ነጻነት ለማድመቅ እየሰሩ መሆናቸውን አብራርተዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሀላፊ ወይዘሮ ትግስት መኳንቴ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ህዝቦች በአንድነትና ጽናት ታግለው የጣሊያንን ወራሪ ሃይል አድዋ ላይ ማሸነፋቸው በነጻነት እንድንኖር አድርገውናል ብለዋል።

በአድዋ ድል አባቶቻችን ምርኮኞችን በመንከባከብና ቁስለኞችን አክሞ በማዳን የሰብአዊነት ጥግ የሆነውን እሴታቸውን ለዓለም ህዝብ ያስተዋወቁበት በመሆኑ ለአሁኑ ትውልድ ትምህርት የሚሰጥ ነው ሲሉም ገለጸዋል።

የባሶና ወራና ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታጠቅ ገድለ አማኑኤል እንደተናገሩት ከአድዋ ፍቅርን፣ ሰላምን፣ አንድነትንና መተባበርን የተማርንበት ነው።

ከመከፋፈልና ጥላቻ ተላቀን የአባቶቻችንን አኩሪ ታሪክ ለመጪው ትውልድ በማስተላለፍ የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ሁሉም መስራት አለበት ብለዋል።

በዩኒቨርስቲው የታሪክ ትምህርት ክፍል የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ሙሉቀን አበበ በበኩሉ በዓሉ አጼሚኒሊክ በትውልድ ስፍራ ለማክበር በመቻሉ ታሪክን አውቆ በእውነት ላይ ተመሰርቶ ለሌሎች ለማስተማር ጠቃሚ እንደሆነ ተናግሯል።

በዓሉ የተከበረው በአጼ-ሚኒሊክ የትውልድ ስፍራ የሚገኙ ታሪካዊ ቅርሶችን በመጎብኘትና ገድሉን በሚያንጸባርቅ የፈረስ ጉግስ ትርኢት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም