ኢዜአ የሚያሳትማት "ነጋሪ" መፅሔት ዝክረ አድዋን በአብይ ጉዳይነት ሠንቃ በድሉ ዋዜማ ለሕትመት በቃች

86

አዲስ አበባ፣ የካቲት 22/2013 ( ኢዜአ)  በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በየሁለት ወራት የምትታተመው "ነጋሪ" መፅሔት 125ኛውን ዝክረ አድዋ በአብይ ጉዳይነት በመዳሰስ በድሉ ዋዜማ እነሆ ለሕትመት በቃች።

በ70 ገጾች የተቀነበበችው መጽሔቷ በድሕረ ሕግ ማስከበር ዘመቻ ስላለው የትግራይ ክልል አሁናዊ ሁኔታ፣ የ2013 አገራዊ ምርጫ እና የውሃ ዲፕሎማሲን በተመለከተም በስፋት ትናገራለች።

ኢዜአ በሁለት ወራት ልዩነት የሚያዘጋጃት "ነጋሪ" መፅሔት በ16ኛ ሕትመቷ የተለመደ የሕትመት ጥራቷን ጠብቃ፣ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ርዕሰ ጉዳዮችን ሠንቃ በአድዋ ድል ዋዜማ ታትማለች።

ነጋሪ የኢትዮጵያዊያን የማንነት ልክ ማሳያና የድል ቁንጮ፣ የዓለም ጭቁን ህዝቦች የነጻነት ቀንዲል የሆነውን መልከ ብዙ፣ ቀለመ ደማቁና አድማስ ዘለሉን አድዋን 'አድዋ የአፍሪካ ፀሐይ' ስትል በፊት ገጿ ዘክራለች።

በዝክረ አድዋ አርዕስቷም የነገረ-አድዋን ተጋድሎና ረቂቅ አሻራ፣ አድዋ በሊቃውንት ብዕር፣ የአድዋ ሰዋዊ፣ አገራዊና ዓለም አቀፋዊነቱን በረከቶች በስፋት ቃኝታለች።

ነጋሪ በወቅታዊ ጉዳዮቿ በትግራይ ክልል ከሕግ ማስከበር ዘመቻ በኋላ ሕዝቡን ወደተረጋጋና ሠላማዊ እንቅሰቃሴ ለመመለስ እየተደረጉ ስላሉ እንቅስቃሴዎች ከጊዜያዊ አስተዳድሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ ጋር የተደረገውን ቃለ ምልልስም አስነብባለች።

ያልተያዙ የፅንፈኛው የህወሓት ቡድን አመራሮችን ለሕግ የማቅረብ ተልዕኮ፣ የመተከልን ጉዳይ ጨምሮ በሌሎች ወቅታዊ፣ አገራዊና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀኔራል ብርሃኑ ጁላን አናግራለች።

በመጪው ወርኅ ግንቦት መጨረሻ የሚካሄደው 6ኛ ዙር አገራዊ ምርጫ ሠላማዊ፣ ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ተዓማኒ እንዲሆን ምልከታዋን በጥልቀት ዳሳለች።

በዲፕሎማሲው ረገድም የዓባይ ውሃ ዙሪያ ገብ አገራዊ ዲፕሎማሲን ጨምሮ የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ታሪክ አውስታለች።

ነጋሪ ከወቅታዊ ጉዳዮች ባለፈም ጤናና ግብርናን ጨምሮ ማኅበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮችን በስፋት በመዳሰስ ለንባብ አብቅታለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም