በወጣቱ ላይ የተሰራውን የጥላቻ ትርክት በትምህርት ስርዓት ማስተካከል ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በወጣቱ ላይ የተሰራውን የጥላቻ ትርክት በትምህርት ስርዓት ማስተካከል ይገባል
አዲስ አበባ፣ የካቲት 22/ 2013 ዓ.ም (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በወጣቱ ላይ የተሰራውን የመለያየትና የጥላቻ ትርክት በትምህርት ስርዓት መመለስ እንደሚገባ ብሔራዊ የወጣቶች ምክክር ጠየቀ።
ይህ የተጠየቀው "በስልጡን ምክክር አዲስ የተስፋ ምዕራፍ" በሚል እየተካሄደ ባለው ብሔራዊ የምክክር መድረክ ላይ ነው።
በመድረኩ ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎችና ከፖለቲካ ፓርቲዎች የተወከሉ ወጣቶች በአገራቸው ጉዳይ ያደረጉት ብሔራዊ ምክክር በተወካያቸው ወጣት ተሰማ ካሳ በኩል ቀርቧል።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ባላቸው የጋራ አጀንዳና አገራዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ የወጣቶች ደህንነት፣ ስራ አጥነትና የትምህርት ጥራት ውይይቱ ያተኮረባቸው ነጥቦች እንደነበሩ ዘርዝሯል።
ቀደም ባሉት ዓመታት በትምህርት ስርዓት የተደገፈ የመለያየትና የጥላቻ ትርክት በወጣቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ማሳደሩን ወጣቶቹ በአጽንኦት ማንሳታቸውን ተወካዩ ገልጿል።
ይህንን ትርክት በማረም የቀና ትውልድ ለመፍጠር በትምህርት ስርዓቱ ያሉ ክፍተቶች መቃኘት እንዳለባቸው ወጣቶቹ ጠይቀዋል።
እንደ ወጣት ተሰማ ገለጻ ነጻና ገለልተኛ የትምህርት ተቋማትን በመገንባት ጥራት ያለውና ዘላቂ የትምህርት ስርዓት መገንባት እንደሚቻል ወጣቶቹ በምክክራቸው አመላክተዋል።
የነበሩ ችግሮችን በማረም የተሻለች ኢትዮጵያን በዘላቂነት ለመገንባት እየተሻሻለ ባለው የትምህርት ስርዓት እንዲታይ ወጣቶች በተወካያቸው በኩል ጠይቀዋል።
በተመሳሳይ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተውጣጡ የተማሪ ተወካዮች ያደረጉትን ውይይት የአርሲ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ህብረት ፕሬዝዳንት ተማሪ ሻሩ ማርቆስ አቅርቧል።
የትምህርት ፖሊሲና ስራ አጥነት፣ የህግ የበላይነትና የማህበራዊ ሚዲያ ተጽእኖ የውይይታቸው ትኩረት እንደነበሩ ገልጿል።
ኢትዮጵያን በምጣኔ ሃብት ልማት የተሻለች የሚያደርጉ ተማሪዎችን ለማፍራት የተቀረጸው የትምህርት ፖሊሲና ስራ አጥነት ትኩረት እንደሚያሻው መጠቆማቸውን አብራርቷል።
በአዲስ አበባ ወዳጅነት አደባባይ እየተካሄደ ባለው የምክክር መድረክ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ከ1 ሺህ 200 በላይ ሰዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
መድረኩ እንደ አገር የሚነሱ የጋራ ችግሮችን በመለየትና የጋራ መፍትሄ በማስቀመጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።