ለትግራይ ክልል መልሶ ግንባታ ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ለትግራይ ክልል መልሶ ግንባታ ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተደረገ
መቀሌ፤ የካቲት 22/ 2013 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር፣ የሐረሪ ክልል እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳዳር ለትግራይ ክልል መልሶ ግንባታ ሥራ ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ።
ድጋፉን በአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ በሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦድሪን በድሪ እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድ ቡህ የተመራ ልዑክ መቀሌ ከተማ ተገኝቶ አስረከቧል፡፡
ልዑካኑ መቀሌ አሉላ አባነጋ አየር ማረፊያ ሲደርስ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች፣ በሃይማኖት አባቶችና በአገር ሽማግሌዎች አቀባበል ተደርጎለታል።
የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮችና የሐረሪ ክልል ለክልሉ ያደረጉት ድጋፍ የአብሮነት መገለጫና የኢትዮጵዊነት ተምሳሌት ነው ተብሏል፡፡
በድጋፍ ርክክቡ ወቅት ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ "ራስ ወዳድ የሆነው የጥፋት ቡድን ባመጣው ችግር በህዝብ ላይ የተለያየ ጉዳት ደርሷል" ብለዋል።
"የዛሬዋ ኢትዮጵያ በዚህ መልክ እንድትቆም የትግራይ ህዝብ ዋጋ ከፍሏል" ያሉት ምክትል ከንቲባዋ፤ ህግ የማስከበር ዘመቻውን ተከትሎ የደረሰውን ጉዳት በኢትዮጵያዊያን ትብብር መጠገን እንደሚቻል አመልክተዋል፡፡
"የከተማ አስተዳዳሩ የትግራይን ህዝብ ጉዳት ሊካፈልና ከጎኑ ለመቆም የፍቅር ስጦታ ይዞ ወደ ትግራይ መጥቷል" በማለትም ነው የገለጹት።
በድጋፍ ርክክቡ ወቅት እንደተገለጸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 100 ሚሊዮን ብር፣ 574 ኮምፒውተሮች፣ 123 ፕሪንተሮችና የፎቶ ኮፒ ማሽኖችን ድጋፍ አድርጓል።
ከዚህ በተጨማሪ አስተዳደሩ ሦስት አምቡላንስ እና ሦስት ተሽከርካሪዎችን ድጋፍ ማድረጉንም ነው ምክትል ከንቲባዋ የገለጹት፡፡
አጠቃላይ በገንዘብና በቁሳቁስ የተደረገው ድጋፍ ከ135 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑን ጠቁመው፤ ድጋፉም ቀጣይነት እንዳለው አመልክተዋል።
የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦድሪን በድሪ በበኩላቸው የክልሉ መንግስትና ህዝብ የአብሮነት፣ የወንድማማችነት እና የኢትዮጵያዊነት መገለጫ የሆነውን ድጋፍ ይዘው ወደ መቀሌ ማቅናታቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ክልሉ 10 ሚሊዮን ብር ፣ አምቡላንስና የተለያየ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አህመድ መሐመድ ቡህ በበኩላቸው አምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
የትግራይ ህዝብ ከገጠመው ችግር እስኪወጣ ድረስ አስተዳደሩ ከጎኑ እንደሚቆምም አረጋግጠዋል፡፡
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ ድጋፉን በተቀበሉበት ወቅት እንዳሉት ክልሉን መልሶ ለመገንባት ሁሉም ሊረባረብ ይገባል፡፡
ጊዜያዊ አስተዳደሩ የትግራይ ክልልን መልሶ ለመገንባት ሥራ መጀመሩን ገልጸው፤ ለዚህም ሁሉም እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል፡፡
"ለአገራችን የሚበጀው ሰላምና መረጋጋት ነው" ያሉት ዶክተር ሙሉ፣ በትግራይ ክልል ከደረሰው ጉዳት ሁሉም ሊማር እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ እንድትበለጽግ ሁሉም የአገሪቱ ህዝቦች ለሰላም ቅድሚያ እንዲሰጡም አሳስበዋል፡፡
የልኡካን ቡድኑ አባላት መቀሌ ከተማ በነበራቸው ቆይታ የአይደር ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን ጎብኝተዋል፡፡