ሳማሪታንስ ፐርስ በትግራይ ለተፈናቀሉ ወገኖች መጠለያ ፕላስቲክ ሸራ እና አምፖል ድጋፍ አደረገ

የካቲት 22 /2013 (ኢዜአ) 'ሳማሪታንስ ፐርስ' የተባለ ግብረሰናይ ድርጅት በትግራይ ክልል በህግ ማስከበር ሂደት ከቀዬአቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ከስምንት ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የፕላስቲክ ሸራ እና በፀሐይ ኃይል የሚሰራ አምስት ሺህ አምፖል ድጋፍ አደረገ፡፡

ድጋፉን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ሙሉ ነጋን ጨምሮ ሌሎች የጊዜያዊ አስተዳደሩ የሥራ ኃላፊዎች ተረክበዋል።

በሳማሪታንስ ፐርስ የኢትዮጵያ ተወካይ ኒክ ቤካርት በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የፕላስቲክ ሸራው ሁለት ሺህ ሰዎችን በጊዜያዊነት ማስጠለል የሚችል ነው።

"ቁሶቹ በህግ ማስከበር ሂደቱ ከቀዬአቸው ተፈናቅለው በተለያዩ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ ወገኖች የሚውሉ ናቸው" ብለዋል፡፡

ድርጅቱ ከዚህ ቀደም በትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው እናቶችና ህጻናት የሚውል ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው አልሚ ምግብ ድጋፍ ማድረጉንም አስታውሰዋል፡፡

ድርጅቱ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉቀን ሃብቱ፤ ድጋፉም በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖች በቀጥታ የሚደርስ መሆኑን አረጋግጠዋል።

"በአሁኑ ወቅት ትግራይ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ትገኛለች" ያሉት ዶክተር ሙሉቀን፤ "ሰውን ለመርዳት ድንበር እንደማይገድብ ከሳማሪታንስ ፐርስ ግብረሰናይ ድርጅት እንማራለን" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም