ቀጥታ፡

ፓርቲዎች ዓላማቸውን ሲያስተዋውቁ ለአካል ጉዳተኞች ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጡ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 22/2013 ዓ.ም(ኢዜአ) በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዓላማቸውን ሲያስተዋውቁ ለአካል ጉዳተኞች ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጡ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ጥሪ አቀረበ።

አካል ጉዳተኞች በአገሪቱ ያላቸው የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲሁም በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ውስን መሆኑ በተለያዩ አጋጣሚዎች ይነገራል፡፡

ለዚህም አካል ጉዳተኞች እንደ አካል ጉዳታቸው አይነት ተገቢውን የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ምቹ መሰረተ ልማት አለመኖር በምክንያትነት ይጠቀሳል፤ ህብረተሰቡ ለአካል ጉዳተኞች ያለው የተዛባ አመለካከትም እንዲሁ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በቀጣይ አገራዊ ምርጫ የአካል ጉዳተኞች የምርጫ ተሳትፎ ምን ይመስላል? ፓርቲዎች ዓላማቸውን ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ ከማድረግ አኳያ እየሰሩ ያለትን ስራና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሚመለከታቸውን አካላት አነጋግሯል።

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ እንዳሉት አካል ጉዳተኞች በቀጣይ አገራዊ ምርጫ ላይ የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዓላማቸው ምን እንደሆነ ማወቅ ይኖርባቸዋል።  

በዚህ ረገድ እስካሁን ድረስ ወደ ፌዴሬሽኑ የመጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች አለመኖራቸውን ገልጸው፣ "ባለፉት ምርጫዎች ሲደረግ እንደነበረው የምርጫ ቀን ሲቃረብ አካል ጉዳተኞች ለቁጥር ብቻ እንዲሳተፉ መቀስቀስ ተገቢ አይሆንም" ብለዋል።

ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ በመጪው አገራዊ ምርጫ የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዓላማቸውን ሲያስተዋውቁ ለአካል ጉዳተኞች ልዩ ትኩረት እንዲሰጡ ጠይቀዋል።

ፓርቲዎቹ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ዓላማቸውን ሲያስተዋውቁ እንደማንኛውም ጤናማ ሰው ሳይሆን የተለያዩ የአካል ጉዳተኞች ያለባቸውን የጉዳት ሁኔታ ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ መሆን እንዳለበትም ገልጸዋል።

አካል ጉዳተኞች በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ፤ መብታቸው እንዲከበር እና የመምረጥ መብታቸው እንዲረጋገጥ ፌዴሬሽኑ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን አቶ አባይነህ ለኢዜአ ገልፀዋል፡፡

በቀጣይም ፌዴሬሽኑ ለአካል ጉዳተኞች የፈለጉትን እና ያመኑበትን ፓርቲ መምረጥ የሚያስችላቸውን የመራጮች ስልጠና እንደሚሰጥም ጠቁመዋል፡፡

እንደ አቶ አባይነህ ገለጻ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ ለማረጋገጥ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡

"የሲቪክ ማህበራት፣ የመንግስት ተቋማት እና የህግ አስከባሪ አካላት ለኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ድጋፍ በማድረግ የመራጮችን ግንዛቤ ለማሳደግ  ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይኖርባቸዋል" ብለዋል፡፡

አካል ጉዳተኞች መራጭ ብቻ ሳይሆኑ ተመራጭ መሆን እንዲችሉም የመመረጥ መብታቸው ሊከበር እንደሚገባም ነው ዋና ዳይሬክተሩ የገለጹት።

በመጪው አገራዊ ምርጫ አካል ጉዳተኞችን ያማከለና ምቹ የምርጫ ቦታ ማዘጋጀት እንደሚገም ነው አቶ አባይነህ ያመለከቱት።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በበኩላቸው በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ለአካል ጉዳተኞች መረጃ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰሩ እና በእቅዳቸው ውስጥ ማካተታቸውን ተናግረዋል፡፡

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ሊቀ-መንበር አቶ ማሙሸት አማረ የምርጫ ቅስቀሳ ሥራ ገና በመጀመር ላይ መሆኑንና በቀጣይ ፓርቲው አካል ጉዳተኞችን ከግምት ባስገባ ሁኔታ ዓላማውን የማስተዋወቅ ሥራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በዚህም ፓርቲው ቢመረጥ ከአካል ጉዳተኞች አንጻር ለመስራት ያሰባቸውን ሥራዎች ለአካል ጉዳተኛ ማህበራትና አካል ጉዳተኞች በብዛት ባሉበት አካባቢ ድረስ በመሄድ በሚገባ የማስተዋወቅ ሥራ እንደሚሰራ አመልክተዋል፡፡ 

"ለአካል ጉዳተኞች በምናደርገው ቅስቀሳ ድጋፍ ለማግኘት ሳይሆን ስለ ፓርቲው ተገቢውን መረጃ ለመስጠት ነው" ሲሉም ነው አቶ ማሙሸት የተናገሩት፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ ፀሐፊ ወይዘሮ መሊሀ ጅሀድ በበኩላቸው ፓርቲያቸው በአሁኑ ወቅት እጩ የማስመዝገብ ሂደት ላይ መሆኑን ገልፀው ሂደቱ እንደተጠናቀቀ የፓርቲውን አቋም እና ፖሊሲ ለአካል ጉዳተኞች ማህበራት የማስተዋወቅ ሥራ ይሰራል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ለተለያዩ አካላት ስልጠናዎችን መስጠት፣ በክልሎች የምርጫ ክልል ቢሮዎችን መክፈት፣ እጩዎች መመዝገብ እና መረጃዎችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ የማድረግ ሥራ እያከናወነ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም