ወጣቱ ከአድዋ አኩሪ ድል በመማር ከድህነት ለመውጣት የሚደረገውን ትግል ማገዝ እንደሚጠበቅበት ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቱ ከአድዋ አኩሪ ድል በመማር ከድህነት ለመውጣት የሚደረገውን ትግል ማገዝ እንደሚጠበቅበት ተገለጸ
ጎባ የካቲት 20/2013 (ኢዜአ) ወጣቱ ትውልድ ጀግኖች አባቶች በአንድነት ተባብረው በአድዋ ከተጎናፀፉት አኩሪ ድል በመማር ከድህነት ለመውጣት የሚደረገውን ትግል ማገዝ እንደሚጠበቅበት ተገለጸ፡፡
ከዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች የተወጣጡ ነዋሪዎች 125ኛው የአድዋ ድል በዓል በባሌ ሮቤ በፓናል ውይይት አክብረዋል፡፡
ተሳታፊዎቹ እንዳሉት የአድዋ ድል ጀግኖች አባቶች ወራሪውን የኢጣሊያን ኃይል ድል በመንሳት ነጻነትን የተቀዳጁበት ታሪካዊ ክስተት ነው፡፡
የአድዋ ድል የኢትጵያዊያን ብቻ ሳይሆን መላው አላም ጥቁር ህዝቦች ጭምር የሚኮሩበት ታሪካዊ የድል በዓል እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ከበዓሉ ተሳታፊዎች መካከል ሻምበል ሻወል መኩሪያ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት አድዋ ጀግኖች አባቶች ሀገራቸውን ለመንጠቅ የመጣውን የፋሽስት ኃይልን በማሳፈር ድል የነሱበት ታሪካዊ ገድል ነው ብለዋል፡፡
የአሁኑ ትውልድ ከጀግኖች አባቶች ልምድ በመውሰድ አንድነቱን በማጠናከር በሀገሪቱ የተጀመሩ የልማት ውጥኖችን ከግብ በማድረስ ሀገሪቱ ከድህነት ለማውጣት የሚደረገውን ትግል ማገዝ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡
የአድዋ ድል ኢትዮጵያዊያን አንድ ከሆኑና ከተባበሩ የማይቀዳጁት ድል እንደሌለ ትልቅ ማሳያ ነው ያሉት ደግሞ ሌላው የበዓሉ ተሳታፊ ሻምበል ሰለሞን አለሙ ናቸው፡፡
ከጥንት አባቶች አኩሪ የጀግንነት ታሪክ የአሁኑ ትውልድ በመማር ለአካባቢው ብሎም ለሃገሩ ሰላምና ልማት ሊተጋ እንደሚገባ አመልክተው ለዚህም የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡
ወይዘሮ ሶፊያ ገዛሊ በበኩላቸው ወጣቱ ትውልድ ጀግኖች አባቶች በአድዋ ከተጎናጸፉት አኩሪ ድል በመማር በድህነትና ኋለቀርነት ለማሸነፍ መትጋት እንደለበት ተናግረዋል፡፡
የባሌ ዞን አስተዳደር ከፍተኛ አመራር አቶ አዱላ ሂርጳዬ እንደገለጹት የአድዋ ድል ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክር ታሪካዊ ክስተት ነው፡፡
ጀግኖች አባቶች ከተቀናጁት ድል በመማር በሀገሪቱ የተጀመሩ ሁለንተናዊ ለውጦች ከግብ ደርሰው ፍሬ እንዲያፈሩ ሁሉም ድርሻውን መወጣት አንዳለበት ተናግረዋል፡፡
የበዓሉ መከበር የኦሮሞ ህዝብ ከሌሎች የሀገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በመተባበር በወራሪ ኃይል ላይ የተቀዳጁት ድል የአሁኑ ትውልድ ተንከባክቦ እንዲጠብቀው ለማድረግ ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው አቶ አዱላ ገልጸዋል፡፡
በተለይ ወጣቶች የአንድነት መገለጫና የጥቁር ሕዝቦች ኩራት ከሆነው የዓድዋ ድል ሕብረትና መተሳሰብን በመማር ለሀገር ሰላምና ቀጣይነት ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።
በበዓሉ አከባበር ሥነ-ሥርዓ የኃይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎች፣ወጣቶች፣ ሴቶችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉ ሲሆን የጀግኖች አባቶችን ገድል የሚዘክሩ ዝግጅቶች ቀርበዋል፡፡