በደቡብ ክልል መጪው ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ዝግጅት እየተደረገ ነው

48

አርባምንጭ ፤የካቲት 20/2013( ኢዜአ) ስድስተኛው አገራዊና ክልላዊ ምርጭ በደቡብ ክልል ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የጸጥታ አስከባሪው ሃይል ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መሆኑ ተገለጸ።

የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምርጫውን ሰላማዊ ለማድረግ የጸጥታ ሀይሉ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት መወጣት እንዲችል ባዘጋጀው ዕቅድ ዙሪያ በአርባምንጭ ከተማ ከዘርፉ አመራሮች ጋር ተወያይቷል።

የቢሮው ሀላፊ አቶ አለማየሁ ባውዴ በዚህ ወቅት እንዳሉት በለውጡ ህዝቡ ያነሳቸውን ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት የሚቻለው ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሲካሄድ ነው።

“የምንገኝበት ወቅት የለውጡ ትሩፋቶች ከሆኑት አንዱ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የሚደረግበት በመሆኑ የጸጥታ ሀይሉ ለየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ሳይወግን በገለልተኝነት መስራት አለበት” ብለዋል።

ስለዚህ ሁላችንም ያለ አንዳች ማመንታት በታማኝነት በመምራት የጸጥታ አስከባሪውን ተቋም በህዝብ ያለውን አመኔታ የበለጠ ማሳደግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ነብዩ ኢሳያስ በበኩላቸው ምርጫው ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ ከማድረግ አንጻር የፖሊስ ሚና ከፍ ያለ ነው ብለዋል።

ለዚህም ምርጫው ተአማኒ እንዲሆንና ፖሊስ በገለልተኝነት ህዝቡን እንዲያገለግል እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ያለው የጸጥታ ሀይል ከህዝቡ ጋር ተቀናጅቶ እንዲሰራ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የክልሉ የጸጥታ ሀይል ህግ የማስከበር  ልምድ ያለው ከመሆኑ አንጻር ለምርጫው ሰላማዊነት ዝግጁ መሆኑን ገለጸው ከቁሳቁስ ጋር ተያይዞ ያሉ ክፍተቶችን ለማሟላት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም