"የአድዋ ድል የአሁኑ ትውልድ ያለበትን አገራዊ ሃላፊነት እንዲያስተውል የሚያስገድደው ነው"...አምባሳደር ሳሚያ ዘካሪያ - ኢዜአ አማርኛ
"የአድዋ ድል የአሁኑ ትውልድ ያለበትን አገራዊ ሃላፊነት እንዲያስተውል የሚያስገድደው ነው"...አምባሳደር ሳሚያ ዘካሪያ
የካቲት 20/2013(ኢዜአ) "የአድዋ ድል የአሁኑ ትውልድ ያለበትን አገራዊ ሃላፊነት እንዲያስተውል የሚያስገድደው ነው" ሲሉ በኳታር የኢትዮጵያ አምባሳደር ሳሚያ ዘካሪያ ገለጹ።
አምባሳደሯ "ኢትዮጵያዊያን እንደ አገር የተጋረጡብንን ፈተናዎች ለማለፍ በጋራ መቆም ይጠበቅብናል" ብለዋል።
በኳታር የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሰራተኞች 125ኛውን የዓድዋ ድል በዓል በዶሃ ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ጋር ከትናንት በስቲያ በበይነ መረብ የውይይት መድረክ አክብረዋል።
የአድዋን ድል የተመለከቱ የመነሻ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እንደተደረገባቸው በዶሃ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።
አምባሳደር ሳሚያ የአድዋን የድል በዓል ስናከብር እንደ ትውልድ ያሉብንን አገራዊ ኃላፊነትና ግዴታ እንድናስተውል ያስገድደናል ብለዋል።
አድዋ ላይ የቅኝ ግዛትና የዘረኝነት አስተሳሰቦችን መንፈስ ድል መምታት እንደተቻለ ሁሉ በዚህም ወቅት አፍራሽ አመለካከቶችን በመመከት ኢትዮጵያዊያን በአንድነት መቆም እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
'አሁን የምንገኝበት ወቅት ኢትዮጵያዊያን ከምንጊዜውም በበለጠ አንድነታችንን በማጠናከር ከፋፋይ የፖለቲካና የዘረኝነት አስተሳሰቦችን ድል መምታት የሚያስፈለግበት ነው' ብለዋል።
ድህነትን ድል በማድረግ እንደ አገር የተጋረጡብንን ፈተናዎች ተወጥተን ዜጎቿ የሚኮሩባት ሕብረ ብሔራዊት አገር በመፍጠር ከአድዋ ዘመን ጀግኖች የላቀ ሚና መጫወት ይኖርብናል ብለዋል አምባሳደሯ።
ለዚህም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታና መሰል ታላላቅ አገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ማጠናከርና አብሮ የመኖር እሴቶችን ማጎልበት ይጠበቅብናል ነው ያሉት።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም ያለፉት ትውልዶች በየአውደ ውጊያው መስዋዕትነት ከፍለው ያቆዩዋትን አገር ሉዓላዊነት መጠበቅ ብቻ ሳይሆን ወደ ብልጽግና ማማ ማድረስ የአሁኑ ትውልድ ሃላፊነት እንደሆነ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያን እንደ አድዋ ዘመን ሁሉ በጠላቶቿም ሆነ በወዳጆቿ በክብር የምትታይ "የአፍሪካ ዕንቁ ማድረግ" የትውልዱ ግዴታ መሆኑን ተናግረዋል።
ለዚህም 'አገሬ ምን ውለታ ትዋልልኝ ከሚል አስተሳሰብ በመውጣት ለአገሬ ምን ውለታ ልዋልላት' ወደሚል አስተሳሰብ መሸጋገር ግድ እንደሚል ገልጸዋል።
ኢትዮጵያዊያኑ የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በማጠናቀቅ እንደ ዓድዋ ድል ትውልድ እየተቀባበለ ለዘመናት የሚዘክረው ታሪክ እንደሚሰሩ መግለጻቸውን ኤምባሲው ገልጿል።
125ኛው የአድዋ ድል በዓል "አድዋ የሕብረ ብሔራዊ አንድነት ዓርማ" በሚል መሪ ሃሳብ ይከበራል።
የዘንድሮው የአድዋ ድል ከየካቲት 1 እስከ 30 ቀን 2013 ዓ.ም በተለያዩ ሁነቶች እንዲከበር በፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የሚመራና በዓሉን የሚያስተባብር የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መቋቋሙ ይታወቃል።