የኢትዮጵያ የባህል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫል ነገ በድሬዳዋ ይጀምራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባህል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫል ነገ በድሬዳዋ ይጀምራል
ድሬዳዋ ፤ የካቲት 20/2013 (ኢዜአ)18ኛ የኢትዮጵያ የባህል ስፖርቶች ውድድርና 14ኛው የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫል በድሬዳዋ አስተዳደር አስተናጋጅነት ነገ እንደሚጀመር ተገለጸ።
በውድድሩ የሚሳተፉ የተለያዩ ክልሎችና ከተማ አስተዳደር ስፖርተኞች ፣ አሰልጣኞችና ቡድን መሪዎች ድሬዳዋ ገብተዋል።
የአስተዳደሩ ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽነር ሻኪር አህመድ በሰጡት መግለጫ "የባህል ስፖርቶችን ለአንድነታችን" በግል መሪ ሃሳብ በሚኪያሄደው ውድድሩ ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ የባህል ስፖርተኞች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ተናገረዋል፡፡
በውድድሩ 11 የባህል ስፖርት ዓይነቶች ውድድሩ እንደሚካሄዱና በዚህም ከሚሳተፉ 829 ስፖርተኞች መካከል 253 ሴቶች መሆናቸውን አመልክተዋል።
ከ2 መቶ በላይ አሰልጣኞችና የቡድን መሪዎችም ተሣታፊ ይሆናሉ ብለዋል፡፡
ከባህል ስፖርቱ በተጨማሪ 14ኛው የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫል እንደሚኪያሄድ ገልፀዋል፡፡
በተጓዳኝም ሶስተኛው ሀገር አቀፍ የጤናና የአካል ብቃት እንቅስቃሴም ይካሄዳል ብለዋል ኮሚሽነሩ፡፡
የኮሮና መከላከያ መመሪያዎች በአግባቡ በስራ ላይ በማዋል የሚኪያሄደው ውድድር የተቀዛቀዘውን የምጣኔ ሃብትና ማህበራዊ መስተጋብርን ለማነቃቃት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተመልክቷል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሙራድ በደዊ ውድድሩን የተሳካ እንዲሆን ለማስቻል ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡
ውድድሩ የድሬዳዋ የቱሪዝም መዳረሻዎች ለማስጎብኘት፣ የርስ በርስ ግንኙነትና የባህል ትውውቅን ለመፍጠር ያስችላል ብለዋል፡፡
በተጨማሪ ስፖርት ፍቅርና አንድነት በማጠናከር ለዘላቂ ሰላምና ልማት ለማነሳሳት እንደሚያግዝም ገልጸዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ባህል ስፖርተኞች ፌደሬሽን ፕሬዘዳንት ወይዘሮ ኢፍቱ አባስ የድሬዳዋ የባህል ስፖርት ቡድን የተሻለ ውጤትና ዋንጫ ለማስመዝገብ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡
ከየካቲት 21 ቀን እስከ የካቲት 27 የሚካሄደው ውድድሩ ተሳታፊዎችን በተገቢው በማስተናገድ የድሬዳዋ ህዝብ የተለመደውን እንግዳ አክባሪና ተቀባይነቱን በተግባር እንዲያሳይ ጥሪ አቅርበዋል፡፡