ቀጥታ፡

ከተማ አስተዳደሩ የሸማች ሕብረት ሥራ ማኅበራትን አቅም ለማጎልበት 500 ሚሊዮን ብር ደጎመ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 19/2013(ኢዜአ) የአዲስ አበባ አስተዳደር በከተማዋ የሚገኙ የሸማቾች ሕብረት ሥራ ማኅበራትን አቅም ለማጎልበት 500 ሚሊዮን ብር መደጎሙን አስታወቀ፡፡

በመዲናዋ ላለው የዋጋ ንረት ዋነኞቹ መንስኤዎች የገበያ አሻጥርና ምርቶችን መሸሸግ መሆኑም ተገልጿል።

አስተዳደሩ በከተማዋ የተስተዋለውን የኑሮ ውድነት ለማቃለል እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችና ህገወጥ ተግባራትን በፈፀሙ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ላይ የተወሰዱ እርምጃዎችን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት በምክትል ከንቲባ አዳነች አበቤ የሚመራ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ዋጋ የማረጋጋት በሁሉም ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች ጭምር እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።

ምክትል ከንቲባዋ በየጊዜው የሚስተዋለው የዋጋ ንረት በመዲናዋ ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ የኑሮ ጫና እያሳደረ መሆኑን ተናግረዋል።

አሁን ላለው የዋጋ ንረት ዋነኛው መንስኤ የገበያ አሻጥር እና የተለያዩ ምርቶችን መሸሸግ መሆኑንም ጠቁመዋል።

እንደ ምክትል ከንቲባዋ ገለጻ ከንግዱና ሸማቹ ማኅበረሰብ ጋር ውይይት በማድረግ የዋጋ ንረትን በጋራ መከላከል በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መግባባት ተፈጥሯል። 

በግብርናና በኢንዱስትሪ በተለይም በእህልና ጥራጥሬ ምርቶች ላይ የተስተዋለውን የዋጋ ንረት ለመከላከል የሸማቾች ሕብረት ሥራ ማኅበራት ምርት እንዲያገኙ መደረጉን ገልፀዋል፡፡

የኑሮ ውድነቱን ለመፍታት ከተማ አስተዳደሩ የሸማች ሕብረት ሥራ ማኅበራትን ለመደገፍና አቅማቸውን ለማጎልበት 500 ሚሊዮን ብር ድጎማ ማድረጉን አስታውቀዋል።

ማኅበራቱ ምርቶችን ከአምራቾች በቀጥታ እንዲያገኙ የማስተሳሰርእና በገበያ ውስጥ ያለውን ማነቆ በዘላቂነት ለመፍታት እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ በሰራው የሕግ ማስከበር ሥራ ሕጉን ጠብቀው በማይንቀሳቀሱ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ላይ እርምጃ መውሰዱንም ምክትል ከንቲባዋ አስታውቀዋል፡፡

በዚህም ከተማ አስተዳደሩ በ200 ሺህ የንግድ ድርጅቶች ላይ ክትትልና ቁጥጥር ማድረጉን ነው የገለጹት።

ከሕግ አግባብ ውጭ ሲንቀሳቀሱ በተገኙ ከ30 ሺህ በላይ የተለያዩ የንግድ ተቋማት ላይ ከጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ጀምሮ የንግድ ፈቃዳቸው እንዲታገድ፣ ድርጅታቸው እንዲታሸግ የተደረጉና ክስ የተመሰረተባቸውም እንዳሉ አስረድተዋል።

በመዲናዋ የዋጋ ንረትን ለመከላከል እየተደረገ ባለው ርብርብ ኅብረተሰቡ ተሳትፎ ከማድረግ ባለፈ ህገወጥ ነጋዴዎች ሲያጋጥሙት ለመንግስት ጥቆማ እንዲያደርገ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ለሸማች ሕብረት ሥራ አቅም ማጎልበቻ የሚሰጠው ድጎማ በአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም በኩል መሆኑ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም