በትግራይ ክልል ወንጀል የፈጸሙ ቡድኖች ከህግ ተጠያቂነት አያመልጡም - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልል ወንጀል የፈጸሙ ቡድኖች ከህግ ተጠያቂነት አያመልጡም
የካቲት 19/2013 (ኢዜአ) በትግራይ ክልል ጾታዊ ጥቃትን ጨምሮ የተለያየ ወንጀል የፈጸሙ ቡድኖች ከህግ ተጠያቂነት እንደማያመልጡ መንግስት ገለጸ።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ሁኔታ ዙሪያ መግለጫ አውጥቷል።
በመግለጫው “የማይታመኑት የህወሃት ወንጀለኞች ቡድን የተሳሳተ መረጃን በመጠቀም ባለፉት ወራት በትግራይ ክልል ያለውን ውስብስብ የጸጥታ፣ የሰብዓዊና ማህበራዊ ፈተና ለመወጣት ጥረት እያደረገ የሚገኘውን ሉዓላዊውን የኢትዮጵያ መንግስት ተወቃሽ ለማድረግ እየሰሩ ነው” ብሏል።
“የመንግስት ጥረት ክልሉን ለማረጋጋትና የዜጎችን ህይወት ወደነበረበት ለመመለስ መንግስት ከሰብዓዊ ድርጅቶችና ከልማት አጋሮች ጋር ይሰራል” ብሏል።
በክልሉ የሰብዓዊ ድጋፍ የሚያደርጉ አካላት እና መገናኛ ብዙሃን ገብተው እንዲሰሩ መፈቀዱን ያስታወሰው መግለጫው፤ የፌዴራል መንግስት ተቋማት ከድርጅቶቹ ጋር በትብብር ለመስራት ያላቸውን ዝግጁነት አረጋግጧል።
በድርጅቶቹ የሚደረገው የሰብዓዊ ድጋፍ በሰላም ሚኒስቴር አስተባባሪነት የሚከናወን መሆኑን ገልጾ፤ በጋራ ስምምነት መሰረት 129 የሁለትዮሽና የባለ ብዙ ድጋፍ ድርጅቶች 135 ሰራተኞች በክልሉ ተንቀሳቅሰው ድጋፍ እንዲሰጡ ፈቃድ እንደተሰጣቸው ጠቁሟል።
“29 ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች ስራ ላይ ሲሆኑ የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ኮሚቴ እና የኮማንድ ፖስት አባል ሆነው እየሰሩ ይገኛሉ” ያለው መግለጫው፤ ኮማንድ ፖስቱ የሚደረገው ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚመለከተው አካል በተዘረጋው መዋቅር በኩል እየደረሰ ስለመሆኑ የሚያረጋግጥ መሆኑን ጠቅሷል።
መግለጫው የሚዲያ ተደራሽነትን በተመለከተ እንደገለጸው፤ ክልሉ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ መሆኑን ታሳቢ ያደረገ የአገር ውስጥና የዓለም ዓቀፍ ሚዲያዎች እንቅስቃሴ ተፈቅዷል።
በክልሉ ሚዲያ እንዳይንቀሳቀስ ተደርጓል መባሉን የሃሰት ውንጀላ መሆኑን ጠቁሟል።
በአሁኑ ወቅት ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ፣ ለአልጀዚራ፣ ለኒውዮርክ ታይምስ፣ ፍራንስ 24፣ ሮይተርስ፣ ቢቢሲና ፋይናንሺያል ታይምስ ፈቃድ የተሰጣቸው መሆኑ ገልጿል።
የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በተመለከተ የጾታ ጥቃትን ጨምሮ የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን ለመመርመር መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን ያመለከተው መግለጫው፤ የወንጀሉን ፈጻሚዎች መንግስት ተከታትሎ ለፍርድ እንደሚያቀርብም አረጋግጧል።
የወንጀሉ ፈጻሚዎች ከህግ እንደማያመልጡና ተገቢው ፍርድ እንደሚሰጣቸው አረጋግጧል።