ቀጥታ፡

የአድዋ ድል ነጮች በጥቁር ህዝቦች ያደርሱ የነበረውን በደልና ጭቆና ያመከነ ነው-- የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር

ባህርዳር የካቲት 19/2013 (ኢዜአ)  የአድዋ ድል ነጮች በጥቁር ህዝቦች ያደርሱ የነበረውን ወደር የለሽ በደል፣ ጭቆናና ብዝበዛ ለማስቀጠል የነበራቸውን ዕቅድ ያመከነ መሆኑን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ብዙነሽ መሰረት ገለጹ።

125ኛው የአድዋ ድል በዓል ''የአድዋ ድል የህብረ ብሄራዊ አንድነት አርማ ነው'' በሚል መሪ ሀሳብ በዓሉ በባህር ዳር ከተማ ድሉን በሚዘክር ውይይት ዛሬ ተከበረ።

በውይይት መድረኩ የተገኙት ሚኒስትር ዴኤታዋ  እንዳሉት፤ የአድዋ ድል በነጮች ዘንድ ታላቅ ድንጋጤን የፈጠረና ሃፍረትን ያከናነበት ቀን ነው።

ግፍ ሲፈፀምባቸው ለነበሩ ጥቁር ህዝቦች ደግሞ ነጭን ማንበርከክና ድል ማረግ እንደሚቻል በተግባር ያሳዩበት እንደሆነም ተናግረዋል።

ጥቁሮች ከሚደርስባቸው ግፍና በደል ነፃ ለመውጣት ለሚያደርጉት ትግል የይቻላልን መንፈስ ያጎናፀፈና ነፃ እንዲወጡ በር የከፈተ ድል መሆኑን ተናግረዋል።

በዓለም መድረክ  የሃገራችን የዘመኑ መሪዎቿና ጀግኖች ህዝቦቿ ስማቸው ከፍ ብሎ እንዲታወቅና የድል አድራጊነት ተምሳሌት ተደርገው እንዲቆጠሩ አድርጓል ብለዋል።

የብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል  ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም አለኽኝ በበኩላቸው የአድዋ ድል በዓለም የተገፉና የተጨቆኑ ህዝቦች ነጻነትን ያጎናጸፈ ገድል መሆኑን ገልጸዋል።

የአድዋ ድል የሁላችን ኢትዮጵያዊያን ድል ቢሆንም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተገዳዳሪ የሌለው ትልቅ የድል በዓል በመሆኑ በቀላሉ ታሪኩ ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል።

ድሉ ለጥቁር ህዝቦች ያጎናጸፈው ነጻነት ተከትሎ የአፍሪካ ህዝቦች አረንጓዴ ፣ቢጫና ቀይ ሰንደቃችንን ወደ ራሳቸው በመውሰድ   አሁንም እየተጠቀሙበት እንደሚገኝ ተናግረዋል።

''አሁናዊ የኢትዮጵያ ማንነትና ቅርፅ የአድዋ ድል ውጤት ነው፤ አድዋን ስናስብ ማንነታችን፣ ከፍታችን፣ ሃይማኖታችን፣ አብሮነታችን፣ ያረጋገጥንበት የድል ቀን ነው ብለዋል።

ድሉ ሁሉም ነጮች በዓለም ላይ የበላይነት ሆነው ይታዩ የነበረው ታሪክ የቀየረ  ታላቅና አኩሪ ገድል  እንደሆነም አስረድተዋል።

አሁንም በጥቃቅን ጉዳዮች ብሄርተኝነት፣ ሰፈርተኝነትና መንደርተኝነት እንዳያሸንፈን በፍቅር ፣በመቻቻልና በአንድነት መቆም ይኖርብናል ሲሉ አብራርተዋል።

''የኢትዮጵያ ገናና ታሪክ እንዲጎላ ያደረገው የአባቶቻችን የአድዋ የድል ገድል ነው'' ያሉት ደግሞ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሙሉቀን አዳነ ናቸው

ልዩነት ሳይኖራቸው ከጫፍ ጫፍ የክተት ጥሪን ተቀብለው ባደረጉት ተጋድሎ እብሪተኛውን የኢጣሊያን ጦር አይቀጡት ቅጣት በመቅጣት የኢትዮጵያን ክብር ከፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

የአሁኑ ትውልድም እርስ በእርስ ከመጠላለፍ ተላቆ የቀደሙ አባቶቹ በአድዋ ድል የፈፀሙትን አኩሪ ገድል በልማቱ በመድገም ሀገሩን ከድህነትና ኋላ ቀርነት ለማላቀቅ በተባበረ ክንድ ጠንክሮ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

ለአድዋ ድል መነሻ የሆኑ ቦታዎችን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግም ቢሮው ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እየሰራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

በበዓሉ አከባበር ሥነ-ሥርዓት የፌዴራልና ክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ አባት አርበኞች፣ ምሁራንና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም