ቀጥታ፡

በመጪዉ አገራዊ ምርጫ የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማሳደግ እየሰራን ነው - የፖለቲካ ፓርቲዎች

የካቲት 19/2013 (ኢዜአ) በመጪዉ አገራዊ ምርጫ የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማሳደግ እየሰሩ መሆኑን ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።

የማኅበራዊ ሳይንስ መምህርን በበኩላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ሴቶችን እንደማሟያ ከመቁጠርና የቁጥር ምጣኔ ከማስቀመጥ ባሻገር ተቋማዊ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉትን መርጠው ማካተት አለባቸው ይላሉ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አገራዊ ምርጫው በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ እንዲከናወን የተለያዩ መርሃ ግብሮች ነድፎ በማስፈፀም ላይ ይገኛል።

በምርጫው የሚሳተፉ ፓርቲዎችም ዕጩዎቻቸውን እስከ የካቲት 21 እንዲያስመዘግቡ ቀነ ገደብ መቀመጡ ይታወቃል።

ፓርቲዎች ሴት ዕጩ ተወዳዳሪዎችን በማስመዝገብ በምርጫው ሁለንተናዊ ሂደት ተሳትፏቸውን ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወኑ መሆኑን ይገልፃሉ።

የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ ወይዘሮ ነቢሃ ሙሃመድ እና የኢትዮጵያ ነጻነት ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ግዛቸው አበራ፤ በምርጫው የሚወዳደሩ ሴት ዕጩዎችን በማስመዝገብ በኩል ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆኑን ገልፀዋል።

የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የማኅበራዊ ሳይንስ መምህር ወይዘሮ መሰረት ተጫኔ ደግሞ በፓርቲዎች ውስጥ ሴቶችን ማካተትን እንደ ትልቅ ግብ ቀርጾ መንቀሳቀስ ብቻውን በቂ አይደለም ይላሉ።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ሴቶችን እንደማሟያ ከመቁጠርና የቁጥር ምጣኔ ከማስቀመጥ ባሻገር ተቋማዊ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉትን መርጠው ማካተት ተገቢ መሆኑን አመላክተዋል።

የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊዋ ወይዘሮ ነቢሃም ፓርቲዎች ሴቶች በፖለቲካ መስክ የነቃ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ጠንክረው መስራት እንዳለባቸው እምነታቸው መሆኑን ገልፀዋል።

ሴቶችን የምናካትተው ለኮታ ሳይሆን መሰረታዊ ለውጥ ማምጣትን ታሳቢ በማድረግ ነው ሲሉም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ነጻነት ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ግዛቸው አበራም ሴቶችን በፖለቲካው መስክ ተሳትፎ የምናሳድገው  ሴቶች "ዘመናዊ አስተሳሰብ፣ ዘመናዊ ኢኮኖሚ፣ ዘመናዊ አገር ይገነባሉ የሚል አስተሳሰብ ስላለን ነው" ብለዋል።

የማኅበራዊ ሳይንስ መምህር ወይዘሮ መሰረት የሴቶችን የነቃ የፖለቲካ ተሳትፎ እንደ እሴት በመቁጠር በራስ መተማመን ያላት ሴት እንድትፈጠር ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።

በመጪው ግንቦት 28 እንደሚካሔድ ቀን ለተቆረጠለት አገራዊ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ካለፈው ሣምንት ጀምሮ የምረጡኝ ቅስቀሳ ዘመቻቸውን ጀምረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም