ቀጥታ፡

በምረጡኝ ቅስቀሳ የሚተላለፉ መልዕክቶች ግጭትና ጥላቻ ቀስቃሽ መሆን የለባቸውም - የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን

የካቲት 19 /2013 (ኢዜአ)  የፖለቲካ ፓርቲዎች በምረጡኝ ቅስቀሳቸው በሚዲያ የሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች ግጭትና ጥላቻ ቀስቃሽ እንዳይሆኑ ሊጠነቀቁ እንደሚገባ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን አሳሰበ።

የፖለቲካ ፓርቲዎች በበኩላቸው የምርጫ ስነ-ምግባር መመሪያውን መርህ በመከተል አማራጭ ፖሊሲዎቻችንን ለሕዝብ እናቀርባለን ብለዋል።

በ6ኛው አገራዊ ጠቅላላ ምርጫ ለመሳተፍ የተመዘገቡ ፓርቲዎች የቅስቀሳ መርሃ ግብር ከየካቲት 8 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በይፋ መካሄድ ጀምሯል።

በዚሁ መሰረት ፓርቲዎች በምረጡኝ ቅስቀሳ መርሃ ግብራቸው አማራጭ ፖሊሲና ስትራቴጂያቸውን በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ለሕዝብ ተደራሽ እያደረጉ ነው።

የፖለቲካ ፓርቲዎች በመገናኛ ብዙሃን በሚያካሂዱት ቅስቀሳ የምርጫ መመሪያውን እንዲከተሉና የሰለጠነ የፖለቲካ ስልት እንዲያራምዱ የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን አንዱዓለም አሳስበዋል።

በመሆኑም በቀጣይ በሚደለደለው የአየር ሠዓት ፓርቲዎች በተለያዩ ጉዳዮች የያዟቸውን አማራጭ ፖሊሲዎች ለሕዝቡ በማስተላለፍ የተመደበላቸውን ጊዜ በአግባቡ እንዲጠቀሙ አሳስበዋል።

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት /መኢአድ/ ፕሬዚዳንት አቶ ማሙሸት አማረ ፓርቲያቸው የምርጫ ስነ ምግባር መመሪያው የሚፈቅደውን መርህ በመከተል አማራጭ ፖሊሲዎቹን ለሕዝብ እንደሚያቀርብ ገልጸዋል።

የምረጡኝ ቅስቀሳው ያልተገባ ምልልስ የማይደረግበትና ሃሳብ በሃሳብ የሚሞገትበት መሆን እንዳለበት የተናገሩት ደግሞ የኅብር ኢትዮጵያ ሊቀመንበር አቶ ግርማ በቀለ ናቸው፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መመሪያ ጥላቻን፣ መቃቃርን፣ አመፃን፣ መለያየትንና ሕገወጥ ድርጊቶችን የሚያደፋፍሩ መልዕክቶች እንዳያወጡ ይመክራል፣ ይቆጣጠራል፡፡

ይህ መመሪያ ተጥሶ ከተገኘ ለጋራ ምክር ቤቱ ሪፖርት በማቅረብ  እርምጃ ማስወሰድ እንደሚቻልም መመሪያው ይጠቁማል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም