ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ የሁለት አጠቃላይ ሆስፒታሎች ግንባታ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 18 /2013 ዓ.ም (ኢዜአ) በአዲስ አበባ በ 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ወጪ የሁለት አጠቃላይ ሆስፒታሎች ግንባታ ተጀመረ፡፡

ግንባታውን የመዲናዋ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤና የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ አስጀምረውታል፡፡ 

በኮልፌ ቀራኒዮና በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተሞች የተጀመሩት ሆስፒታሎቹ በአንድ ዓመት ተኩል ግንባታቸው እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል።

እያንዳንዳቻው 374 አልጋዎች የሚኖራቸው ሆስፒታሎች ግንባታ ሲጠናቀቅ ለ3 ሚሊዮን የአዲስ አበባና አካባቢዋ ነዋሪዎች አገልግሎት እንደሚሰጡ ምክትል ከንቲባዋ ተናግረዋል።

ይህም በመሃል ከተማ የሚታየውን የሆስፒታሎች መጨናነቅ ያቃልላል ብለዋል።

ለሆስፒታሎቹ ግንባታ ከሰባት ዓመት በፊት የመሰረት ድንጋይ ቢቀመጥም ግንባታቸው ሳይጀመር ከመቆየቱም በላይ፤ የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች እንዲነሱ መደረጉን ምክትል ከንቲባዋ ገልጸዋል።

የከተማ አስተዳደሩ አመራር ለአካባቢዎቹ ሕዝብ ጤና አገልግሎት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት የሆስፒታሎቹን ግንባታ አስጀምሯል ብለዋል።

ከተማዋን የጤና ቱሪዝም ማዕከል የሚያደርጉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም አክለዋል።

አስተዳደሩ ከነዋሪዎች ጋር በመቀናጀት ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ምክትል ከንቲባዋ ገልጸዋል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው የአገሪቷን የጤና አገልግሎት አሰጣጥና ተደራሽነት ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የጤና ሚኒስቴር የከተማው አስተዳደር የጤና አገልግሎትን ለማዳረስ የሚያደርገውን ጥረት እንደሚደግፍም አረጋግጠዋል።

የሆስፒታሎቹን ግንባታ የሚያካሂደው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ዮናስ አያሌው ሆስፒታሎቹን ከተያዘላቸው ጊዜ አስቀድሞ ለማጠናቀቅ ይሰራል ብለዋል።

የሆስፒታሎቹ ግንባታ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ የአካበቢዎቹ ነዋሪዎች ትብብር እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም