ቀጥታ፡

የቤተ-ክርስቲያን አባቶች በጋራ ባለመስራታቸው በርካታ የሰላም ትርፍ አጥተናል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

አዲስ አበባ ሐምሌ 20/2010 በኢትዮጵያና በአሜሪካ በሚኖሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን አባቶች መካከል ተፈጥሮ በነበረው ችግር አገሪቱ በርካታ የቅርስና የሰላም ትርፍ ማጣቷን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሜሪካ በመገኘት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ የነበረውን የረዥም ጊዜ ችግር ለመፍታት እርቅ እንዲወርድ አድርገዋል። ቤተ-ክርስቲያኗ በርካታ ተከታዮች ያላትና በአገራዊ፣ ድንበር ተሻጋሪ የሰላም ችግሮች  እና በሌሎችም ጉዳዮች ትልቅ ሚና የነበራት ቢሆንም ሁለቱ ሲኖዶሶች ሳይስማሙ በመቆየታቸው ይህን በጎ ተግባር በአግባቡ እንዳትተገብር አድርጓታል ብለዋል። በመሆኑም የእርቅ ስነ-ስርዓቱ ለእምነቱ ተከታዮች ብቻ ሳይሆን ለማንኛውም ኢትዮጵያዊና ከኢትዮጵያ ውጭ ለሚኖር ህዝብ ትልቅ ብስራት ነው ሲሉም ገልፀዋል።  "የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን በአንድነቷ ቀጥላ ቢሆን ኖሮ የኢትዮጵያና ኤርትራ እንዲሁም ሌሎች ግጭቶችን ለመፍታት ረዥም ጊዜ ባልወሰደ" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከእርቁ በኋላ ብዙ እንጠብቃለን ሲሉ ተደምጠዋል። ከዚህ በኋላ በውጭና በአገር ወስጥ የሚኖሩ የቤተ-ክርስቲያኗ አባቶች ለአንዲት ቤተ-ክርስቲያን በአንድ ሲኖዶስ እንዲተዳደሩ ተወስኗል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም