ቦርዱ ለምርጫ ማስፈጸሚያ የሚውሉ 22 ተሽከርካሪዎችን ከውሮፓ ህብረት ተረከበ

87

አዲስ አበባ፣ የካቲት 18 /2013 ዓ.ም (ኢዜአ)  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ2013 አገራዊ ምርጫ ማስፈጸሚያ የሚውሉ 22 ተሽከርካሪዎች ከአውሮፓ ህብረት ተበረከተለት።

ህብረቱ ተሽከርካሪዎቹን ለቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ አስረክቧል።

አውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ ድጋፍ ሰጪ ልዑካን ቡድን መሪ ኤሪክ ሃበርስ በኢትዮጵያ ፍትሃዊና ተዓማኒ ምርጫ እንዲካሄድ ድርጅቱ ጽኑ ፍላጎት እንዳለው ገልጸዋል።

ምርጫው ስኬታማ ሆኖ እንዲፈጸም አስፈላጊ ግብዓቶችን በመስጠት ህብረቱ አጋርነቱን አሳይቷል ብለዋል።

ከድጋፉ መካከልም ህብረቱ ከጀርመን መንግሥት ያገኛቸውን ተሽከርካሪዎች ለቦርዱ ማበርከቱን ተናግረዋል።

ተሽከርካሪዎቹ 12 ላንድ ክሩዘር እና 10 ቶዮታ ሲሆኑ ለመስክ ሥራና ግብዓቶችን ለማጓጓዝ አገልግሎት እንደሚውሉ ገልፀዋል።

የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን በበኩላቸው አገራዊ ምርጫውን ለማካሄድ የዕጩዎች ምዝገባና መሰል ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸው፤ ለምርጫ ስኬት ግብዓቶች እንደሚያስፈልጉ ተናግረዋል።

ተሽከርካሪዎቹ የቦርዱን አቅም ከማጎልበትና ተልዕኮውን በብቃት ከመፈጸም አኳያ በአስፈላጊና ወሳኝ ወቅት የተገኙና የላቀ ፋይዳም እንዳላቸው ተናግረዋል።

ተሽከርካሪዎቹ የምርጫ ግብዓቶችን ወደ ምርጫ ጣቢያዎች በማጓጓዝ አስተዋጽኦ ያበረክታሉም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም