ቀጥታ፡

የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድሩ የኢትዮጵያን ጥቅም አስጠብቆ እንዲጠናቀቅ እንሰራለን... አምባሳደሮች

የካቲት 18/2013(ኢዜአ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር የኢትዮጵያን ጥቅም አስጠብቆ እንዲጠናቀቅ እንደሚሰሩ በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ እና በሴኔጋል የኢትዮጰያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደሮች ተናገሩ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት አምባሳደሮች የአፍሪካ ህብረትና ሌሎች ተቋማት ግድቡን በተመለከተ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ ንቁ ተሳታፊ እንደሚሆኑም አረጋግጠዋል።

በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ወይንሸት ታደለ ግድቡ የህልውና ጉዳይ እንደመሆኑ ''የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስጠበቅ በትጋት እሰራለሁ'' ብለዋል።

ቀደም ሲል ኢትዮጵያ ግብጽና ሱዳን በአፍሪካ ህብረት በኩል የጀመሩት የሶስትዮሽ ድርድር በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ እልባት ማግኘት ባይችልም መልካም ጅምር ነበር ብለዋል።

ድርድሩ የሶስቱንም አገሮች ብሄራዊ ጥቅም ባስጠበቀ መንገድ እንዲጠናቀቅ የተጣለባቸውን የዲፕሎማሲ ሃላፊነት እንደሚወጡም ነው የሚናገሩት።

የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ፌሊክ ሼሴኬዲ ከተያዘው ወር ጀምሮ የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ሆነው መሾማቸው ይታወሳል።

ፕሬዚዳንቱ ቀደም ሲል በደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ስሪል ራማፎሳ  መሪነት የተጀመረው ሶስትዮሽ ድርድር ውጤታማ እንዲሆን ይሰራሉ ተብሎም ይጠበቃልም ብለዋል አምባሳደሯ።  

ለዚህ ደግሞ ግድቡን በሚመለከት በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ ንቁ ተሳታፊ በመሆን የኢትዮጵያን ጥቅም እንደሚያስጠብቁ አምባሳደር ወይንሸት ገልጸዋል።

በተለይም በተያዘው ዓመት መጨረሻ ግድቡ ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት የሚይዝ በመሆኑ የአፍሪካ ህብረትና አባል አገሮቹ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ በቅርበት እንሰራለን ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1960 በኮንጎ ኪንሻሳ የነበረው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ቢዘጋም በድጋሚ ለመክፈት አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያና ኮንጎ በሰላም ማስከበር ዘርፍ ያላቸው ግንኙነት በኢኮኖሚውና በማህበራዊ ዘርፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚሰሩ መሆኑንም አምባሳደሯ አረጋግጠዋል።

በሴኔጋል የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር መላኩ ለገሰ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከሴኔጋል ጋር ያላትን የረጅም ጊዜ ግንኙነት ወደተሻለ ትብብር ለመቀየር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

"የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላ አፍሪካ ትልቅ ኩራት በመሆኑ አገሮች ከፉክክር ይልቅ በትብብር መንፈስ ከሰሩ ከመልማት የሚያግዳቸው እንዳማይኖር አስረዳለሁ" ነው ያሉት።

ግድቡ የጋራ ተጠቃሚነትን መርህ በማድረግ የተገነባና በተለይም ኢትዮጵያ ዜጎቿን ከድህነት ለማውጣት በራሷ አቅም የምትገነባው መሆኑን የተፋሰሱ አገሮች እንዲገነዘቡ ለማድረግ እንደሚሰሩም ነው የተናገሩት።

በአፍሪካ የሚፈጠሩ አለመግባባቶች መፈታት ያለባቸው በራሳቸው አፍሪካዊያን ነው ያሉት አምባሳደሩ።

ለዚህ ደግሞ የአፍሪካ ህብረት የያዘው መርህ ውጤታማ እንዲሆን በየአገሮቹ ያሉ አምባሳደሮች የተጣለባቸውን ሃላፊነት ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

ለአፍሪካ ብልጽግና አገሮቹ በትብብር የመስራት ልምዳቸውን እንዲያጠናክሩም ከሌሎች አገሮች ዲፕሎማቶች ጋር እንሰራለን በማለትም ገልጸዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2015 በኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን መሪዎች በኩል በተፈረመው የመርህ ስምምነት መሰረት የውሃ ሙሌቱ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ይሞላል።

ባለፈው ዓመት የመጀመሪያው ዙር አራት ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ የያዘ ሲሆን በተያዘው ዓመት ማጠቃለያ ሁለተኛው ዙር 13 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ እንደሚይዝ ይጠበቃል።

የግድቡ ሁለት ተርባይኖችም የኤሌክትሪክ ማመንጨት ሙከራ ይጀምራሉ ተብሎም ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም