ቀጥታ፡

የኦሬንጅ ኩባንያ በአፍሪካ ሦስተኛ የዲጂታል ማዕከሉን ዛሬ በአዲስ አበባ ከፈተ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 18/2013 ( ኢዜአ) የኦሬንጅ ኩባንያ በአፍሪካ ሦስተኛ የዲጂታል ማዕከሉን ዛሬ በአዲስ አበባ ከፈተ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር አብርሃም በላይ ማዕከሉን መርቀው ከፍተውታል።

ማዕከሉ በጎሮ አይ.ሲ.ቲ ፓርክ 500 ሜትር ስኩዬር ሜትር መሬት ላይ አርፏል።

ይህ ማዕከል መተግበሪያዎችን /አፕሊኬሽን/ ለሚሰሩና የፈጠራ ውጤት ያላቸው ደግሞ ወደ ምርት የሚለወጡባቸው ስልጠና የሚሰጥበት ነው።

በተለይም ለምህንድስና ተማሪዎች ተግባር ተኮር ሥራዎችን ለመከወን ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተገልጿል።

ማዕከሉን ወደ ሥራ ለማስገባት የኢትዮጵያ መንግሥት ከጀርመን የልማት ድርጅት /ጂ.አይ.ዜድ/ ጋር መሥራቱ በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ ተወስቷል።

የዲጂታል ማዕከሉ የፈጠራ ክህሎትን ከማሳደግ ባለፈ ወጣቶች በቴክኖሎጂ መስክ ልምድ እንዲያካብቱ ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ተመልክቷል።

በማዕከሉ ከክፍያ ነጻ 90 በመቶ ተግባር ተኮር ሥልጠና እንደሚሰጥ ተገልጿል።

ዶክተር አብርሃም እንደገለፁትም መንግሥት የአገሪቷን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ወደ ዲጂታል ለማሳደግ ከፖሊሲ ጀምሮ ማሻሻያዎችን እያደረገ ነው።

ሚኒስትሩ የማዕከሉ መከፈት በዘርፉ ለሚከናወኑ ተግባራት ጠቀሜታው የላቀ እንደሆነ፤ በተለይም ቴክኖሎጂ ላይ የተመረኮዘ የሥራ ዕድል ፈጠራ ትኩረት እንደተሰጠው አመልክተዋል።

በዚህ ረገድ በማዕከሉ የሚሰጠው ስልጠና ፋይዳ እንዳለው የጠቀሱት ሚኒስትሩ የግሉን ዘርፍ ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚው ለማስገባትም የብዙ አካላትን ትብብር እንደሚጠይቅ አመልክተዋል።

ማዕከሉ ልምድና ለእድገት ወሳኝ የሆኑ ተሞክሮዎች የሚቀሰምበት መሆኑን የገለጹት ዶክተር አብርሃም ኢትዮጵያ በመምጣት በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ መሰማራቱ የሚበረታታ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ በበኩላቸው ቴክኖሎጂን ጨምሮ በኢትዮጵያ ኢንቨስት የሚያደርጉ የውጭ ኩባንያዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ ባለብሩህ አዕምሮ ወጣቶች አገር መሆኗ ቴክኖሎጂን የሚያስፋፋ አሰራር ከመዘርጋት ጋር ተዳምሮ የማዕከሉ ሥራ ውጤታማ እንደሚሆን እምነታቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቴፈን አወር አንድን አገር ወደ ዲጂታል በማሸጋገር በሕዝቡ ሕይወት ላይ እውነተኛ ለውጥ እንደሚመጣ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያም በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ታግዛ ከድህነት ለመውጣት ምርትና ምርታማነቷን ማሳደግ ይኖርባታል ብለዋል።

ኦሬንጅ ኩባንያ በአፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ በሚገኙ 18 አገራት የሚንቀሳቀስ ሲሆን፤ ከ128 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችም አሉት።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም