ቀጥታ፡

በግልገል በለስ ከተማ የሕዝብ ለሕዝብ የሠላም ጉባዔና የእርቀ ሠላም ሥነ-ሥርዓት ተካሄደ

የካቲት 18/2013( ኢዜአ) የመተከል ዞን መቀመጫ በሆነችው ግልገል በለስ ከተማ የሕዝብ ለሕዝብ የሠላም ጉባዔና የእርቀ ሠላም ሥነ-ሥርዓት ተካሄደ።

በሠላም ኮንፈረንስና እርቀ ሠላም መርሃ ግብሩ በዞኑ ሠላምና ጸጥታ በማስከበር ላይ የሚገኘው የተቀናጀ ግብረ ኃይል አመራሮችና የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ታድመዋል።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ በአካባቢው አጋጥሞ የነበረው የጸጥታ ችግር እንዳይቀጥል ሁሉም በየኃይማኖቱ ቃለ መሃላ የፈፀመ ሲሆን፤ በአካባቢው ባህል መሰረት በግ ታርዶ እርቀ ሠላም ተከናውኗል።

የሠላም ጉባዔው ተሳታፊዎች በግልገል በለስ ከተማም ይሁን በዞኑ የተፈጠረው ችግር የሕዝቡ ሳይሆን የተቀነባበረ የጠላት ሴራ እንደሆነ ተናግረዋል።

ችግሩ ከሕዝብ የመነጨ ባለመሆኑም በዞኑ ለሶስት ዓመታት ገደማ የቆየው የሠላም እጦት እየተቃለለ እንደሆነ ገልፀዋል።

የጉባዔው ተሳታፊዎች በእነዚህ ዓመታት የልማት ሥራዎች መቋረጣቸውን አንስተው አሁን በዞኑ አንጻራዊ ሠላም በመታየቱ ሕዝቡ በረሃብና በችግር እንዳይጎዳ የተቋረጡ የልማት ሥራዎች እንዲቀጥሉላቸው ጠይቀዋል።

የመንግሥት ሠራተኛውና አርሶ አደሩ  በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራው እንዲገባ መንግሥት ድጋፍ እንዲያደርግ አመልክተዋል።

የግልገል በለስ ከንቲባ አቶ ሀብታሙ ባልታ ከተማዋ ኢትዮጵያዊያን በአብሮነት የሚኖሩባት በመሆኗ ነዋሪዎቿ ሠላሟን ለመጠበቅና የልማት ሥራዎችን ለማስቀጠል ከአስተዳደሩ ጎን እንዲቆሙ ጠይቀዋል።

ሠላም የሚያደፈርሱ ሃሳቦችና ድርጊቶች ተቀባይነት እንዳያገኙ መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል።

በተቀናጀ ግብረ ኃይሉ የኮማንድ ፖስት ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል አሥራት ዴኔሮ መንግስት የተቋረጡ የልማት ስራዎችን ለማስቀጠል ጥረት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ኮማንድ ፖስቱ ከሁሉም በፊት መቅደም ያለበትን ሠላም በማስጠበቅ አበረታች ውጤቶች እያስገኘ እንደሆነም ገልጸዋል።

ባጋጠመው የሠላም እጦት የተቋረጡ የመሰረተ ልማት ሥራዎች በቅርቡ እንዲቀጥሉ ይደረጋል ብለዋል።

በዞኑ ሠላምና ጸጥታ እያስከበረ የሚገኘው የተቀናጀ ግብረ ኃይል በተለያዩ አካባቢዎች የሕዝብ ለሕዝብ የሠላም ጉባዔና የእርቀ ሠላም ሥነ ሥርዓቶችን በማካሄድ ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም