ቀጥታ፡

የአድዋ ድል በዓልን በአድዋ ከተማ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው-የትግራይ ክልል የማዕከላዊ ዞን አስተዳደር

አዲስ አበባ፣ የካቲት 18/2013 ዓ.ም (ኢዜአ) 125ኛውን የአድዋ ድል በዓል በአድዋ ከተማ በማክበር የአይበገሬነት ተምሳሌት ለመሆን ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ በትግራይ ክልል የማዕከላዊ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።


በትግራይ ክልል የማዕከላዊ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኔ ገብረጻዲቅ እንደገለጹት በትግራይ ክልል ከተካሄደው የህግ ማስከበር ጋር ተያይዞ ህዝቡ አስቸጋሪ ጊዜዎችን አሳልፏል፡፡

ሆኖም በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያዊያን ኩራት የሆነውን የአድዋ ድል በዓል በአድዋ ከተማ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአድዋ አካባቢ ያለው የሰላም ሁኔታ አስቸጋሪ ነው በሚል ህብረተሰቡ መስጋት እንደሌለበትም ጠቁመዋል፡፡

የትግራይ ህዝብ ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር ችግር ቢያጋጥመውም ይህን በዓል በደመቀ ሁኔታ ያከብራል ነው ያሉት፡፡

"በችግር ውስጥ ሆነንም የዘንድሮውን የአድዋ ድል በዓል በደመቀ ሁኔታ በማክበር  የአይበገሬነት ተምሳሌት እንሆናለን " ሲሉም በመግለጽ፡፡  

በዓሉ ያለ አንዳች የጸጥታ ስጋት እንዲከበርም ህብረተሰቡ የአካባቢውን ሰላም ተባብሮ መጠበቅ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የዞኑ አስተዳደርም በአድዋ ከተማ በዓሉን ለማክበር ከሌሎች የመንግስት ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የአድዋ ድል በዓል በሁሉም የኢትዮጵያ አካካቢዎች እየተከበረ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም