የኢንጅነር ስመኘው በቀለ መሞት የግድቡን ግንባታ አያደናቅፈውም...የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የኢንጅነር ስመኘው በቀለ መሞት የግድቡን ግንባታ አያደናቅፈውም...የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች
ጎንደር ሀምሌ 20/2010 የፅናትና የቁጭት ተምሳሌት የነበሩት የኢንጂነር ስመኘው በቀለ ድንገተኛ ሞት የጀመሩትን ታላቅ ስራ ወደ ኋላ እንደማያስቀረው አስትያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ። ነዋሪዎቹ በግድያው ላይ የሚደረገው ምርመራው በፍጥነት ተጠናቆ ፍትህ እንዲሰጥበት ጠይቀዋል። ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል የከተማው ነዋሪ አቶ ሞላ ባዩ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በታሪኳ የጀግኖች መፍለቂያ በመሆኑዋ ኢንጂነር ስመኘው በሞት ቢለዩም በርካታ ተተኪ ጀግኖች አሏት። "የኢትዮጵያ ህዝብ የህዳሴውን ግድብ ግንባታ የጀመረው ለዘመናት በነበረው እልህና ቁጭት በመሆኑ የኢንጂነሩ ሞት የግድቡን ግንባታ ያስተጓጉለዋል የሚሉ ወገኖች ካሉ ታሪካዊ ስህተት የፈጸሙ ናቸው" ብለዋል፡፡ "የኢንጂነሩን አሟሟት መንግስት በአስቸኳይ አጣርቶ ለህዝቡ ይፋ በማድረግ ወንጀለኞችንም ለፍርድ ማቅረብ አለበት" ያሉት ደግሞ ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ሰለሞን መንግስቴ ናቸው። "በኢንጂነሩ ድንገተኛ ሞት እኔም ሆንኩ የከተማው ነዋሪ ልባችን በሀዘን ተሰብሯል" ያሉት አቶ ሰለሞን "ታሪካዊ ጠላቶቻችን ምን ግዜም በእኛ እድገትና ብልጽግና ሴራ ከመሸረብ ወደ ኋላ የሚሉ ባለመሆናቸው ለውጡ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት" ብለዋል፡፡ "ኢንጂነር ስመኘው በኢትዮጵያ ትልቅ የታሪክ ምእራፍ የሚሰጠውን የታላቁን የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከግብ ለማድረስ በከፍተኛ ሀገራዊ ስሜት የዜግነት ግዴታቸውን ሲወጡ የቆዩ ናቸው" ያለው ደግሞ ወጣት ይግዛው ማሞ ነው፡፡ እሳቸው ለዛሬው ወጣት ትውልድ የአይበገሬነትና የጽናት ተምሳሌነት መሆናቸውን በመግለጽ ሞታቸውን የሰማው በከፍተኛ ድንጋጤ መሆኑን ተናግሯል። "የኢንጂነሩ ግድያ በሀገራችን የተጀመረውን ህዝባዊ ለውጥ ለማደናቀፍ ሆን ተብሎ የተሸረበ ሴራ ነው የሚል እምነት አለኝ" በማለት ምርመራው ተጠናቆ በግድያው ላይ እጃቸው ያለ አካላት ተገቢው ፍርድ እንዲሰጣቸው ጠይቋል። "ባከናወኑት አኩሪ ተግባር ከመቃብር በላይ ስማቸው ከፍ ብሎ የሚጠራው ኢንጂነር ስመኘው ለእኔ ከጀግናም በላይ ጀግና ናቸው" ያለው ደግሞ የከተማው ነዋሪ ወጣት ሲሳይ ሰለሞን ነው። የህዳሴው ግድብ የመላው ኢትዮጵያውያን አሻራ ያረፈበት ዘመን ተሻጋሪ የትውልድ ቅርስ እንደመሆኑ ኢንጂነር ስመኘው የሀገራችን ባለውለታና በህዝቡ ልብ ውስጥ ሲታወሱ የሚኖሩ እንደሆኑም ተናግሯል። የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ትናንት ማምሻውን በኢንጂነሩ ድንገተኛ ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ወደ ጎዳናዎች በመውጣትና የተለያዩ መፈክሮችን ያሰሙ ሲሆን ምርመራው ተጠናቆ አፋጣኝ ፍትሕ እንዲሰጥበትም ጠይቀዋል።