ቀጥታ፡

የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽ/ቤት አመራሮች በትግራይ ክልልና በመተከል ዞን ለሰብዓዊ ድጋፍ የሚውል ከወር ደሞዛቸው 50 በመቶ ለገሱ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 18/2013(ኢዜአ) የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽ/ቤት አመራሮች በትግራይ ክልልና በመተከል ዞን ሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ከወር ደሞዛቸው 50 በመቶ ለገሱ።

መንግስት የተጎዱ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም፣ ሰብዓዊ እርዳታን ለማዳረስና የህብረተሰቡን የእለት ተእለት ኑሮ ሰላማዊና የተረጋጋ ለማድረግ ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ በመሆኑ ለውጦች መታየታቸውንም የፓርቲው ሕዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ሃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ለኢዜአ ገልጸዋል።

የፌደራል መንግስት፣ የክልል መንግስታትና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ድጋፍ እንዲያደርጉ በተላለፈው ጥሪ መሠረት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎችን ጨምሮ የክልል መንግስታት፣ ተቋማትና ግለሰቦች ድጋፍ እያደረጉ እንደሆነም አስታውቀዋል።

በጥሪው መሰረትም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለትግራይ ክልል መልሶ ግንባታ የሚውል የአንድ ወር ደሞዛቸውን፣ ከመደመር መጽሐፍ ሽያጭ 200 ሺህ ብር እንዲሁም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በኩል ሦስት የውኃ ማመላለሻ ባለታንከር መኪናዎችን መደገፋቸውን ባለፈው ሳምንት ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ህዝብ በትግራይ ክልልና በቤኒሻንጉል ክልል መተከል ዞን ለችግር የተጋለጡ ዜጎችን ለመደገፍ እያደረገ ያለው ርብርብ የሚበረታታና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው ሃላፊው የገለጹት።

መንግስት በህግ ማስከበር ዘመቻው ምክንያት ሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች እርዳታ እንዲደርስ፣ የተጎዱ መሰረተ ልማቶች ተጠግነው አገልግሎት እንዲሰጡና ህብረተሰቡ በዘላቂነት እንዲቋቋም ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑ ይታወቃል ሲሉ ዶክተር ቢቂላ ገልፀዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮችም መንግስትና ህብረተሰቡ ለወገኖቹ ለመድረስ እያደረገ ያለውን ርብርብ ለማበረታታት የአንድ ወር ወር ደሞዛቸውን 50 በመቶ መለገሳቸውን የገለጹት ዶክተር ቢቂላ ፤የዜጎች መደበኛ ህይወት እስኪስተካከል ድረስ በየደረጃው ያለው አመራር የሚጠበቅበትን እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ዋናው ጽ/ቤት አመራሮች የልማት ሥራዎችንም በመደገፍ አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑንና ከዚህ በፊት ለገበታ ለሀገር ፕሮጀክት የአንድ ወር ደሞዝ መለገሳቸውን ሃላፊው ገልጸዋል።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም