በጋምቤላ ክልል የውጭ ሀገር ገንዘብና የጦር መሳሪያ ሲያዘዋውሩ የተገኙ አምስት ተጠርጣሪዎች ተያዙ

572

ጋምቤላ ፤ የካቲት 18/2013(ኢዜአ) የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ከ300 ሺህ በላይ የውጭ ሀገር ገንዝብ እና ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ሲያዘዋውሩ የተገኙ አምስት ተጠርጣሪዎች መያዙን አስታወቀ።

የክልሉ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ቱት ኮር ለኢዜአ እንደገለጹት ተጠርጣሪዎቹ የተያዙት ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ ባለፉት ሶስት ቀናት ውስጥ በጋምቤላ ከተማ፣ ዲማና ኢታንግ ወረዳዎች በተደረገው ክትትል ነው።

በዚህም ከ300 ሺህ በላይ የደቡብ ሱዳን "ፎን" ገንዘብ ፣ሶስት የክላሽንኮቭ እና አንድ ብሬን ጠብንጃዎች፣ አንድ ሽጉጥ እንዲሁም 90 የብሬንና ዲሽቃ ተተኳሽ ጥይቶች ከተጠርጣሪዎቹ እጅ መገኘታቸውን አስታውቀዋል።

ተጠርጣሪዎች በአሁኑ ወቅት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው እየተደረገባቸው ያለው የምርመራ ሂደት እንደተጠናቀቀም ጉዳያቸው ወደ ፍርድ ቤት የሚላክ ይሆናል ብለዋል።

ኮሚሽኑ ባለፉት ስድስት ወራት ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመግታት ባደረገው ጥረት 315 የክልሸንኮቭ እና ሁለት የብሬን ጠብንጃዎች እንዲሁም አንድ ሺህ 790 የተለያዩ ተተኳሽ ጥይቶችን በቁጥጥር ስር መዋሉንም አውስተዋል።

የህዝቡን ተሳትፎ በማጠናከር ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውሩን ለመግታት የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም