ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች ማህበር ተመሰረተ

የካቲት 17/2013(ኢዜአ) ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ወጣቶችን ያካተተ የኢትዮጵያ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች ማህበር በአዲስ አበባ ተመሰረተ።

ማህበሩ ምስረታውን አስመልክቶ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሀን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተገለጸው፣ ማህበሩ የሥራ ፈጣሪዎችን ችግር በመለየት የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥና ማማከር ላይ አተኩሮ ይሰራል።

ወጣት ሥራ ፈጣሪዎችን መንግስታዊም ሆነ መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር የማስተሳሰር፣ ለወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃዎችን የመስጠት ሥራም ይሰራል ተብሏል።

በተጨማሪም ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች በአገር በቀል ፕሮጀክቶች ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ፣ ለሥራ ፈጠራ የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ እንዲያገኙ፣ ህግና አዋጆች ከመጽደቃቸው በፊት ወጣቶች እንዲሳተፉባቸው ለማድረግ እንደሚሰራም ተገልጿል።

የማህበሩ ፕሬዚዳንትና መስራች ወጣት ሳሚያ አብዱልቃድር በዚህ ወቅት እንደገለጸችው ማህበሩ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ኤጀንሲ ህጋዊ ፈቃድ አግኝቶ የተመሰረተ ነው፡፡

ማህበሩ ከሁሉም ክልሎች የተወጣጡ 500 ወጣቶች በጋራ ሆነው የመሰረቱት እንደሆነና ነባርና አዳዲስ ሥራ ፈጣሪዎችን ማካተቱን ተናግራለች፡፡

ማህበሩ ከሥራ ፈጠራ ባለፈ በስነ ምግባር የታነፀ ትውልድን ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ በትምህርት ቤቶችና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እንደሚሰራም ወጣት ሳሚያ ገልፃለች፡፡

ማህበራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣትም አረጋዊያን፣ አቅመ ደካሞችንና የተቸገሩ ወገኞችን የመርዳት ዓላማ እንዳለውም ተናግራለች፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም