ቀጥታ፡

የጤና ሙያ ማህበራት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በመከላከልና በመቆጣጠር የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን የጤና ሚኒስትሯ ገለጹ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 17/2013(ኢዜአ) የጤና ሙያ ማህበራት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ተናገሩ።

የማህበራቱን ተሳትፎ ለማጠናከር የሁለትዮሽ ስምምነት እንደሚፈርምም ገልጸዋል።

የጤና ሚኒስቴርና የጤና ሙያ ማህበራት የጋራ ምክክር መድረክ ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

ሚኒስትሯ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት ማህበራቱ በዘርፉ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነበር።

ማህበራቱ የአገሪቱ የጤና ሥርዓትን ለማሻሻል እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦ ጉልህ መሆኑን አመልክተዋል።

ሚኒስቴሩ የዘርፉን ችግሮችን ለማቃለል፣ ተነሳሽነታቸው የጨመረና ክህሎታቸው የዳበሩ ባለሙያዎች ለመፍጠር 40 ከሚሆኑ ማህበራት ጋር በመስራት ላይ ይገኛል ብለዋል። 

ማህበራቱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን በመከላከልና በመቆጣጠር ያደረጉት ሙያዊ ድጋፍ በአብነት እንደሚጠቀስ  ዶክተር ሊያ ገልጸዋል።

ከሚኒስቴሩ ጋር በመቀናጀትም ከስምንት ሺህ በላይ ለሚሆኑ ባለሙያዎች ስልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል።

ማህበራቱ በዘርፉ ያላቸውን ተሳትፎ ለማጠናከር የሁለትዮሽ ስምምነት ለመፈራረም መታቀዱንም ሚኒስትሯ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር ተወካይ ሲስተር አስቴር ተሾመ ማህበራቸው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ከጤና ሚኒስቴርና ከሌሎች 10 ማህበራት ጋር ተቀናጅቶ  በመሥራት  ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በቀጣይም ሁሉም የሙያ ማህበራት የሚወከሉበት ምክር ቤት ለማቋቋም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አካባቢ ጤና አጠባበቅ ባለሙያዎች ማህበርን የወከሉት አቶ ተክሉ ኃይሉ ማህበራቸው ከሚኒስቴሩ ጋር በመቀናጀት የኮቪድ-19 መመሪያዎችና ማኑዋሎችን የማዘጋጀትና የማማከር ተግባራት ማከናወኑን አስታውቀዋል።

በቀጣይ ከ11 የጤና ሙያ ማህበራት ጋር በመተባበር ለጤናና ለድጋፍ ሰጪ ባለሙያዎች ስልጠና ይሰጣል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም