የወልድያና አካባቢው ነዋሪዎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለለውጥ አመራሩ ያላቸውን ድጋፍ በሰላማዊ ሰልፍ ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የወልድያና አካባቢው ነዋሪዎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለለውጥ አመራሩ ያላቸውን ድጋፍ በሰላማዊ ሰልፍ ገለጹ
ወልድያ፣ የካቲት 17/2013 (ኢዜአ) -የወልዲያ ከተማና አካበቢው ነዋሪዎች ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይና ለለውጡ አመራር ያላቸውን ድጋፍ ዛሬ ባካሄዱት ሰላማዊ ሰልፍ ገለፀ።
ሰልፈኞቹ በጁንታው ርዝራዦች ለውጡ አይደናቀፍም፤ የአማራን ሕዝብ ጥያቄ በመመለስ ላይ ያለው ብልጽግና ነው፤ የህግ ማስከበር ዘመቻውን በብቃት መርቶ ለድል ያበቃው ብልጽግና ፓርቲ ነው የሚሉና መሰል መፈክሮችን በማሰማት ድጋፋቸውን ገልጸዋል።
ከሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ጠቅል ንጉሴ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት "ለዶክተር አብይና ለለውጡ አመራር ያለንን ህዝባዊ ወገንተኝነት ለማሳየት ሰልፍ ወጥተናል" ብለዋል።
"ለ27 ዓመታት ህዝብን ሲጨቁን የቆየውን ጁንታ በማስወገድ በኩል ትልቅ ሚና ለተጫወተው ብልጽግና ፓርቲና አመራሩን ለመደገፍ ሰልፍ ወጥተናል" ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ጊዜወርቅ ታደሰ ናቸው ።
"በዶክተር አብይና በእርሳቸው በሚመራው ፓርቲና መንግስት የመጣውን ሀገራዊ ለውጥ ለማስቀጠል ዝግጁ ነን " ሲሉ ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።
በመጭው ምርጫ የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አላማቸውን በሰላማዊ መንገድ ለሕዝብ በማቅረብ ለሀገር አንድነትና ለሰላም መስፈን ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ ነዋሪዎቹ አስገንዝበዋል ።
የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወልደትንሣኤ መኮንን በድጋፍ ሰልፉ ላይ ባደረጉት ንግግር የጁንታውን ሃይል በማስወገድ ሂደት ህዝቡ በተለይም ወጣቱ ክፍል የራሱን አስተዋጾ አበርክቷል።
"በዘንድሮ ሀገራዊ ምርጫ ሕዝቡ ህብረ ብሔራዊ የሆነውን ብልጽግና ፓርቲን በመምረጥ ለውጡን ሊያስቀጥል ይገባል " ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የወልድያ ከተማ ከንቲባ አቶ መሀመድ ያሲን በበኩላቸው ወጣቱ ለሀገር አንድነትና ለሕዝብ ጥቅም እየሰራ ያለውን ብልጽግና ፓርቲን በመምረጥ ተጠቃሚነቱን ሊያረጋግጥ ይገባል ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል።
በድጋፍ ሰልፉ ከወልዲያ ከተማና አካባቢው የተውጣጡ ወጣቶችና ሴቶች ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።