ቀጥታ፡

የአድዋ ድል ታላቁ የህዳሴ ግድብን የመሠለ አስደናቂ ታሪክ ለመስራት ያነሳሳ ነው ---ዶክተር ሂሩት ካሳው

አሶሳ፣ የካቲት 17 / 2013(ኢዜአ) የአድዋ ድል ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የመሠለ አስደናቂ ታሪክ ለመስራት ያነሳሳ አኩሪ ገድል መሆኑን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው ተናገሩ፡፡

125ኛው የአድዋ ድል  በዓል በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ደረጃ ዛሬ በአሶሳ ከተማ ተከብሯል፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው  በዚህ ወቅት እንዳሉት የአድዋ ድል ታሪክ የጥቁር ህዝቦች ታሪክ ምሰሶ ነው፤ ኢትዮጵያውያን አንገታቸው ቀና አድርገው እንዲጓዙ አድርጓል፡፡

ጀግኖች አባቶች  ብዙ ሆነው እንደ አንድ ጥላትን ያንበረከኩበትን የአድዋ ታሪካዊ ድል ባያስመዘግቡ ኢትዮጵያም ሆነች ሌላው የአፍሪካ ሀገራት አሁን ያለውን ላይመስሉ ይችሉ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

በተለይ ሀገራችን የራሷ ቋንቋ ፣ቱባ ባህል እና ታሪክ አይኖራትም ነበር ብለዋል፡፡ 

ዛሬም የራሳችን የምንለው እሴት መሠረት የአድዋ ድል ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም ሲሉም  ዶክተር ሂሩት ገልጸዋል፡፡

አባቶች በማይመች ጊዜ እና ሁኔታ ፈታኝ ችግሮችን ተሻግረው ዛሬ በኩራት የምንናገርበትን ታሪክ አስረክበው አልፈዋል ያሉት ሚኒስትሯ የአሁኑ ትውልድ ከዚህ ሊማር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የምንገኝ  ደግሞ ፈተናዎችን ተጋፍጠን የጀመርነው የህዳሴ ግድብ ወደ ፍጻሜ እያደረስን ነው፤ ይህም የአሁኑ ትውልድ ታሪክ እየሠራ መሆኑን ያሳየ ነው ብለዋል፡፡

የአድዋ ድል ባይመዘገብ ኖሮ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የመሠለ አስደናቂ ታሪክ ለመስራት ባልተነሳሳን ነበር ሲሉም ሚኒስትሯ አብራርተዋል፡፡

ምክንያት እየፈጠሩ ሊለያዩን ከሚፈልጉ የዘመናችን ጠላቶች እና የወሬ ነጋዴዎች ራሳችንን፣ ወገኖቻችንን እና ሃገራችንን መጠበቅ አለብን ብለዋል፡፡

ታሪክ የሚያስረዳን  ወደቁ ሲሉን ተነስተን ታሪክ የምንሠራ አስገራሚ ህዝቦች መሆናችንን ነው ያሉት ዶክተር ሂሩት ይህም ለትውልድ ተጠብቆ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡ በዚህ ረገድ ብዙ መስራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን የአድዋ ኢትዮጵያውያን አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲጓዙ ያደረገ ታሪካዊ ድል መሆኑን ተናግረው ዓድዋ ሲነሳ አብሮ የሚጠቀሰው የአባቶቻችን የአንድነት ምስጢር ነው ብለዋል፡፡

ዛሬም እንደ አድዋ በአንድ ልብ እንድንነሳ የሚስገድዱን በርካታ ጉዳዮች እንዳሉ ልብ ማለት ያስፈልገናል ሲሉ ርዕሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል፡፡

ጥቃቅን ልዩነቶቻችን በማየት የተዳከምን የመሰላቸው ሀገራት አባይን የመጠቀም መብታችንን ለመጋፋት ወረራ ሊፈጽሙ ሞክረዋል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የአድዋን ድል መሠረት በማድረግ ለሃገራችን ሉአላዊነት መከበር ዘብ መቆም አለብን ሲሉ አሳስበዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ወይዘሪት ምስኪያ አብደላ በበኩላቸው  ሃገር ተረካቢ ወጣቶች ስለሃገራቸው ትክክለኛ ታሪክ ማወቃቸው  በኢትዮጵያ ግንባታ ጥረቶች ውስጥ የድርሻቸውን እንዲወጡ እንደሚስችላቸው ገልጸዋል፡፡

ከክልሉ ከተማ አሶሳ በቅርብ ርቀት የሚገኘው ታሪካዊ ስፍራ "የአድዋ መታሰቢያ ፓርክ” ተብሎ እንደሚሰየምም ሃላፊዋ አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም