የግልግል ዳኝነትና የእርቅ አሠራር ስርአት ለንግዱ ማህበረሰብ ፋይዳው ከፍያለ ነው-ምክር ቤቱ - ኢዜአ አማርኛ
የግልግል ዳኝነትና የእርቅ አሠራር ስርአት ለንግዱ ማህበረሰብ ፋይዳው ከፍያለ ነው-ምክር ቤቱ
አዳማ፣ የካቲት 17/2013/ኢዜአ/ የግልግል ዳኝነትና የእርቅ አሠራር ስርዓት ለንግዱ ማህበረሰብ ፋይዳው ከፍያለ መሆኑን የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አስታወቀ።
ኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዝን ፌሎሺፕ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በግልግል ዳኝነት ዙሪያ ያዘጋጀው የምክክር መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል።
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳት ኢንጅነር መላኩ እዘዘው በወቅቱ እንደገለጹት የግልግል ዳኝነትና የእርቅ አሠራር ስርአት ለንግዱ ማህበረሰብ ፋይዳው ከፍያለ ነው ።
"የግልግል ዳኝነትና የእርቅ አሠራር ስርአት መኖሩ በንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሁም በመሰል ዘርፎች የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በመፍታት ተከራካሪ ወገኖች ህጋዊ መብትና ጥቅም እንዲያገኙ አድርጓል" ብለዋል።
ኢትዮጵያ ተቀብላ ያጸደቀችው አለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት ስምምነት ለነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ማደግ ከፍያለ አስተዋፆኦ እንዳለው ተናግረዋል።
የንግዱ ማህበረሰብን አስመልክቶ በመደበኛው ፍርድ ቤት በሚደረግ የክርክር ሂደት የሚጠፋን ጊዜና ገንዘብ የሚቀንስ በመሆኑ ጠቀሜታው ከፍ ያለ መሆኑን አመልክተዋል።
የምክር ቤቱ ዋና ፀሐፊ አቶ የሱፍ አደምኑር በበኩላቸው ምክር ቤቱ ቀደም ብሎ የግልግል ዳኝነት ማእከል በማቋቋም በንግዱ ማህበረሰብ መካከል የሚከሰቱ አለመግባባቶችን ለመፍታት ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል።
"ነገር ግን ግልፅ የሆነ አዋጅና ደንብ ባለመኖሩ ሂደቱ በተፋጠነ መንገድ እንዳይከናወን አድርጓል" ብለዋል።
አሁን ላይ በግልግል ዳኝነት ላይ የነበሩ ችግሮችን ሊያቃልል የሚችል አዋጅ በመውጣቱ የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚቻል አመላክተዋል።
ምክር ቤቱ ባለፋት ሁለት አመታት በግልግል ዳኝነት ከ30 በላይ በንግዱ ማህበረሰብ ለተፈጠሩ አለመግባባቶች ውሳኔ መስጠቱን አቶ የሱፍ አደምኑር ተናግረዋል ።
በግልግል ዳኝነትና በእርቅ አሰራር ከተፈቱ ጉዳዮች መካከል በኮንስትራክሽን ዘርፍ በአከራይና ተከራይ እንዲሁም በአቅራቢዎችና አከፋፋዮች መካከል የተነሱ አለመግባባቶችን ለአብነት ጠቅሰዋል።
በፌደራል አቃቢ ህግ የማስረጃና የስነ- ስርአት ህግ ፕሮጀክት ዳይሬክተር ወይዘሮ ትእግስት መሐብ በበኩላቸው የግልግል ዳኝነት ስርአት በንግዱ ማህበረሰብ ለሚነሱ አለመግባባቶች በተቀላጠፈ መልኩ ምላሽና ውሳኔ የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።
የአሰራር ስርአቱ በአቃቢ ህግና በፍርድ ቤቶች ላይ የሚደርስ የስራ ጫናን የሚቀንስ መሆኑን አመልክተዋል።
"የግልግል ስርአቱ በደንብና አዋጅ የተደገፈ አሰራር ስለተበጀለት የታለመለትን ግብ ያሳካል" ያሉት ዳይሬክተሯ "ነገር ግን በግልግል ዳኝነት የማይታዩ ጉዳዩች አሉ" ሲሉም ተናግረዋል።
የወንጀል፣ የታክስና ግብር፣ የሸማቾች ጥበቃ፣ የሊዝና ሌሎች ጉዳዮች በፍርድ ቤት የሚወሰኑ መሆኑን ዳይሬክተሯ ለአብነት ጠቅሰዋል ።
ለሁለት ቀን በሚቆየው የምክክር መድረክ የንግዱ ማህበረሰብና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።