የአድዋ ድል ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው የነበራቸውን ክብርና አንድነት የሚያሳይ ቋሚ ማስታወሻ ነው - ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ - ኢዜአ አማርኛ
የአድዋ ድል ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው የነበራቸውን ክብርና አንድነት የሚያሳይ ቋሚ ማስታወሻ ነው - ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 17 ቀን 2013 (ኢዜአ) "የአድዋ ድል ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው የነበራቸውን ክብርና አንድነት የሚያሳይ ቋሚ ማስታወሻ ነው" ሲሉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ ተናገሩ።
የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ማህተም፤ የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ተጋድሎ ቀንዲል ነው።
ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ የአድዋ ድል ኢትዮጵያዊን ረጅም ርቀት በመጓዝ የመጣውን ወራሪ ሃይል በማሸነፍ ድል የተቀዳጁበት መሆኑን ይገልጻሉ።
እንደ ሃይማኖትም ሆነ ሰውኛ የሰው ልጅ ትልቅ ክብር የሚሰጠው ፍጡር መሆኑን በመረዳት ቅኝ ለመግዛት የመጣውን ሃይል ህልም ማክሸፍ መቻል ደግሞ የአንድነትና ለአገር ክብር መቆምን የሚያሳይ እንደነበር አውስተዋል።
"ኢትዮጵያዊያን የተለያየ ቋንቋ፣ መልክና የፊት ገጽታ ይኑራቸው እንጂ መሰረተ ጽኑዋን አገራቸውን ለመንካት የመጣ ማንኛውንም ሃይል ለመመከት ወደኋላ እንደማይሉ አድዋ ማሳያ ነው" ብለዋል።
ድሉ የዓላማ ጽናትን ያሳየ ቋሚ ማስታወሻ እንደሆነ ተናግረዋል።
አድዋ የደከሙ የሚመስሉ የኢትዮጵያ ገጽታዎችን በማቃናት ኢትዮጵያን በዓለም እንድትታወቅ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።
ጥቁር አፍሪካዊያን የኢትዮጵያ ማስታወሻ ይሆናቸው ዘንድ የኢትዮጵያ አምላክ የሚል ቤተ-እምነት እስከ መመስረት መድረሳቸውን አስረድተዋል።
አድዋ የጥቁር ህዝቦች ነጻነት አቀንቃኞች ተስፋ የፈነጠቀ ታላቅ ድል እንደነበር ተናግረዋል።
አድዋ ለኢትዮጵያዊያን የሰጣቸው ቱርፋቶች እንዳለ ሁሉ የተሸነፉ ወራሪዎች የተለያየ ትርክት በመፍጠር ለመበታተን መስራታቸውንም ተናግረዋል።
"ኢትዮጵያዊያን አንድነት፣ መከባበር፣ መዋደድና መተሳሰብ አሸናፊ ያደርጋልና የበደልና የመገፋፋት ስሜትን ማስወገድ ይኖርባቸዋል" ሲሉ መክረዋል።
አገርን ለማስቀጠልም ቀደምት አባቶች ሲያከናውኑት የነበረውን የመተሳሰብና የአንድነት መንፈስ ትምህርት ሰጭ ክስተት እንደሆነም አክለዋል።