የኢንጂነር ስመኘው ሞት መንስኤ በአፋጣኝ አንዲጣራ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ጠየቁ - ኢዜአ አማርኛ
የኢንጂነር ስመኘው ሞት መንስኤ በአፋጣኝ አንዲጣራ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ጠየቁ
አዲስ አበባ ሀምሌ19/2010 በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞት መንስኤ በአስቸኳይ ተጣርቶ ለህዝብ ይፋ እንዲደረግ አስተያየታቸውን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሰጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተናገሩ። አስተያየት ሰጪዎቹ በኢንጂነር ስመኘው ሞት ማዘናቸውን ገልጸው የሞታቸውን መንስኤ ለማወቅ ለሚደረገው ጥረት አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርጉም አረጋግጠዋል። ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ዛሬ ጠዋት በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ መኪናቸው ውስጥ ሞተው መገኘታቸው የሚታወስ ነው። ይህ አሳዛኝ ዜና ከተሰማበት ሰዓት አንስቶ ፖሊስ በስፍራው በመገኘት ምርምራ እያካሄደ ሲሆን በምርመራው መሰረትም ኢንጂነሩ የሞቱት በጥይት መሆኑን አረጋግጧል። ነዋሪዎቹ በሰጡት አስተያየት በኢንጂነር ስመኘው ላይ በደረሰው የሞት አደጋ ሃዘናቸው ጥልቅ እንደሆነ ገልፀው ፖሊስ አሟሟታቸውን ለማጣራት ከምንግዜውም በተሻለ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ጠይቀዋል። የከተማው ነዋሪ አቶ በለጠ ጣራ እንደተናገሩት ኢንጅነር ስመኘው በቀለ የመላው ኢትዮጵያ 100 ሚሊዬን ህዝብ አባት ሲሆኑ የበለጸጉት አገራት ሄዶ መስራት የሚችሉ ነገር ግን ከወገኑ ጋር ኖሮ ቆላ ደጋ ሲንከራተት የኖሩ መሆኑን ተናግረው ዛሬ እዚህ አደባባይ ላይ መገኘቱ በጣም ጥልቅ ሃዘን ነው የሚሰማው ብለዋል። ወጣት ዳንኤል አበበ በበኩሉ ወጣቱ እንግዲህ የሞታቸውን መንስኤ ለማወቅ በመሚደረገወው ጥረት አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ እንዳለበት ጠቁሞ ፤ ወንጀሉን ለመከላከል እና ወጣቱ ሌላ ነገር እንዳይሰማው ወደ ሌላ አቅጣጫ እንዳያመራ የማረጋጋት ስራ ቢሰራ ጥሩ ነው ብሏል። የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል ዘይኑ ጀማል የኢንጅነር ስመኘውን አሟሟት አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ ፖሊስ ጉዳዩን ለማጣራት የሚያስችለውን መረጃ እንዳሰባሰበ ገልጸዋል። ኮሚሽነሩ አክለውም ሞታቸው በጥይት እንደሆነም አረጋግጠው የፖሊስ አባላትም በቀጣይ አሟሟቱን ለማጣራት ርብርብ እያደረጉ እንደሆነም ተናግረዋል። ኢንጅነር ስመኘው በቀለ መስከረም 3 ቀን 1957 ዓ.ም በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ልዩ ስሙ ማክሰኝት በተባለ ቦታ ነው የተወለዱት። ከ1978 እስከ 1991 ዓ.ም በኢትዮዽያ ኤሌክትሪክ ኋይል ኮርፖሬሽን ኮተቤ በሚገኘው ማሰልጠኛ ኢንስቲዩት በሙያቸው አገልግለዋል ። ከ1991 እስከ 1992 በኢጅነሪንግ ዲፓርትመንት በሲቪል ምህንድስና ሰርተዋል። ከ1997 እስከ 2002 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ደግሞ በግልገል ጊቤ ፕሮጀክት ሲያገለግሉ ቆይተዋል። በዚሁም የግልገል ጊቤ 2 ፕሮጀክት ማኔጀር በመሆን ሰርተዋል። ከ2003ዓ.ም ጀምሮ ህይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ደግሞ የብዙ ኢትዮዽያዊያን የድካም ውጤትና ተስፋ በሆነው የታላቁ ኢትዮያጵያ ህዳሴ ግድብ ዋና ስራ አስኪያጅ ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል።