ኮርፖሬሽኑ ለትግራይ ክልል መልሶ ማቋቋሚያ አምስት ሚሊዮን ብር አበረከተ - ኢዜአ አማርኛ
ኮርፖሬሽኑ ለትግራይ ክልል መልሶ ማቋቋሚያ አምስት ሚሊዮን ብር አበረከተ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 17/2013(ኢዜአ) የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ለትግራይ ክልል መልሶ ማቋቋሚያ የአምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ።
ኮርፖሬሽኑ ባለፉት ሁለት ዓመታት ለማህበራዊ ኃላፊነት 450 ሚሊዮን ብር መስጠቱንም ገልጿል።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ረሺድ ከማል ድጋፉን ለትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ፣ ለትግራይ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ዶክተር አብርሃም በላይ እና ለጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮች አስረክበዋል።
በርክክቡ ወቅት አቶ ረሺድ እንዳሉት ኮርፖሬሽኑ ሌሎቹን መርዳት ቀርቶ ለራሱም የሕልውና ችግር እንደነበረበት ገልጸው፤ ከሶስት ዓመታት ወዲህ ተቋማዊ ሪፎርም በማድረግ ከተረጂነት ወጥቶ ትርፋማ እየሆነ መጥቷል።
በዚህም ተቋማዊ ሕልውናውን በማጠናከር ከራሱ ተልዕኮ ባሻገር ከሚያገኘው ትርፍ ሀብት በተለያዩ መስኮች ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።
ኮርፖሬሽኑ የሕዝብ ሀብት በመሆኑ ከባለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ 450 ሚሊዮን ብር ለማህበራዊ ኃላፊነት ማዋሉን ተናግረዋል።
ለአብነትም በኮቪድ 19 ወረርሺኝ ለደንበኞቹ የስድስት ወራት 50 በመቶ የቤት ኪራይ ቅናሽ በማድረግ 370 ሚሊዮን ብር የሚገመት እገዛ ማድረጉን፣ ቫይረሱን ለመከላከል ለሚከናወን ተግባርም 10 ሚሊዮን ብር ማውጣቱን አስታውቀዋል።
ለገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ደግሞ ማኔጅመንቱና ሰራተኞቹ 20 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገዋል ማድረጋቸውን ገልጸው፤ ለሜቄዶኒያ የአረጋዊያንና የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል አምስት ሚሊዮን ብር፣ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 20 ሚሊዮን ብር፤ እንዲሁም ለአገር መከላከያ ሰራዊት ሁለት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል።
መንግስት ትግራይን መልሶ ለማቋቋም ባደረገው ጥሪ መሰረትም በዛሬው ዕለት ለትግራይ ህዝብ ያለውን አጋርነት ለማሳየት የአምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለማድረግ መወሰኑን ገልፀዋል።
በቀጣይም ኮርፖሬሽኑ በትግራይ ያለው ሁኔታ እስኪሻሻል ድረስ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እና 'ገበታ ለሀገር' የመሳሰሉ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያን በኢኮኖሚው መስክ ለመለወጥ ወሳኝ እንደሆኑ ገልጸው፤ ፕሮጀክቶቹ ከግብ እንዲደርሱ ግለሰቦችና ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ በበኩላቸው በክልሉ የተደረገውን ህግ የማስከበር ተልዕኮ ተከትሎ በክልሉ ችግሮች መኖራቸውን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት ክልሉን መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የቤቶች ኮርፖሬሽን ያደረገው ድጋፍ ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ትልቅ አቅም ነው ሲሉም ገልፀዋል።
ከዚህም ባሻገር የትግራይ ህዝብ በችግር ጊዜ አለኝታ እንዳለው የሚያረጋግጥበት እንደሆነም ነው ያስረዱት።
በፌዴራልና በክልል መንግስታት ተቋማት እየተደረጉ ያሉ ድጋፎች ለህዝብ አብሮነትና አንድነት መጎልበት ትልቅ መልዕክት እንዳለው ጠቁመዋል።
የትግራይ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ዶክተር አብርሀም በላይ በበኩላቸው የትግራይ መልሶ ማቋቋም ስራ የሁሉንም ኢትዮጵያዊ የጋራ ጥረት እንደሚጠይቅ ገልፀዋል።
በመሆኑም ሁሉም ዜጋ ለትግራይ ህዝብ አለኝታነቱን እንዲያሳይ ጠይቀዋል።