የባህል ስፖርቶች በትምህርት ሥርዓት ውስጥ ሊካተቱ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የባህል ስፖርቶች በትምህርት ሥርዓት ውስጥ ሊካተቱ ነው
አዲስ አበባ፣ የካቲት 17/2013 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ መገለጫ የሆኑ የባህል ስፖርቶችን በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ለማካተት እየተሰራ መሆኑን የባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን አስታወቀ ።
በዓለም አቀፍ ውድድሮች ተሳትፎን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑንም ገልጿል።
የባህል ስፖርቶች ከክርስቶስ ልደት በፊት በስድስተኛውና ሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመናት ይዘወተሩ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያመለክታሉ።
ከክርስቶስ ልደት በኋላም በኢትዮጵያ ነገሥታት፣ መሣፍንት፣ ሹማምንት፣ ሎሌዎችና ሕዝቡም በውድድሮች ይሳተፍ ነበር። ለመሸናነፍ በሚደረጉ ፉክክሮችም ሕዝብ ይዝናናባቸው እንደነበር ተጽፏል፡፡
በኢትዮጵያ ገበጣ፣ ገና፣ ፈረስ ጉግስና የቀስት ዒላማን ጨምሮ 294 የባህል የስፖርት ዓይነቶች እንደሚገኙ ተፈራ መኮንን የተባሉ የባህል ስፖርት ተመራማሪ ያካሄዱት ጥናት ያሳያል።
ከነዚህ የባህል ስፖርቶች መካከል 11ዱ ሕግና ደንብ ወጥቶላቸው በአገር አቀፍና በክልሎች ደረጃ ውድድር እንደሚካሄድባቸው መረጃዎች ያመለክታሉ።
ገበጣ፣ ገና፣ ፈረስ ጉግስ፣ የቀስት ውድድር፣ ኩርቦ፣ ቡብና ሻህ ሕግና ደንብ ወጥቶላቸው ከሚካሄዱ የባህል ስፖርቶች መካከል ይጠቀሳሉ።
የባህል ስፖርቶችን በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ለማካተት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ የባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ሰለሞን አስፋው ለኢዜአ አስታውቀዋል።
ፕሬዚዳንቱ እንደሚያስረዱት ፌዴሬሽኑ ከዩኒቨርሲቲዎች የስፖርት ትምህርት ክፍሎች ጋር በመቀናጀት እንቅስቃሴ ጀምሯል።
በተለይም ከኮተቤ ሜትሮፖሊቲያን ዩኒቨርሲቲ ጋር የተጀመረው እንቅስቃሴ በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል ብለዋል።
ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመቀናጀት ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ለተውጣጡ መምህራን በአሰልጣኝነት፣ በዳኝነትና በባህል ስፖርቶች ምንነትና ሕጎች ላይ ያተኮረ ሥልጠና መሰጠቱን እንደ ማሳያ አቅርበዋል።
በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ትምህርት ክፍል ውስጥ የባህል ስፖርቶች እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት ከተካተተ ሁለት ዓመታት ማስቆጠሩን ፕሬዚዳንቱ አስታውሰዋል።
አገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ የባህል ፌስቲቫሎች ያላትን ተሳትፎ ለማሳደግ ስፖንሰሮች እየተፈላለጉ መሆኑንና በስፖርቶቹ ላይ ያለውን አመለካከት ለመቀየር ጥረት እተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ እስካሁን የተሳተፈችባቸው ዓለም አቀፍ ፌስቲቫሎች ከሶስት እንደማይበልጡ በማስታወስ።
በአዲስ አበባ ከተማ ስፖርቶቹ ሕዝባዊ መሰረት እንዲኖራቸው ከታዳጊዎች ጀምሮ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፣ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውድድር ለማድረግ ታስቧል ብለዋል።
ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2016 በብራዚል በተካሄደው በመጀመሪያው የዓለም የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫል “ኮርቦ” በሚባለው የባህል ስፖርት በሁለት ተወዳዳሪዎች ተሳትፋለች።
አምና ካናዳ ለሁለተኛ ጊዜ ታስተናግደዋለች ተብሎ በነበረው ፌስቲቫል ለመሳተፍ ዝግጅት እየተደረገ ቢሆንም፤ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ሳይካሄድ ቀርቷል።
የዓለም የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫል በየአራት ዓመቱ ይከናወናል።