ቀጥታ፡

የጉባ ወረዳ አመራር ድርብ አገራዊ ኃላፊነት እንዳለበት አውቆ መስራት አለበት-የተቀናጀ ግብረ ኃይል

የካቲት 17/2013  ( ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የሚገኘውን የጉባ ወረዳን የሚያስተዳደረው አመራር ድርብ አገራዊ ኃላፊነት እንዳለበት አውቆ ጠንክሮ መስራት አለበት ሲል የተቀናጀ ግብረ ኃይል አሳሰበ።

የጉባ ወረዳ የኢትዮጵያ ትልቁ ፕሮጀክት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እየተከናወነ ያለበት ስፍራ እንዲሁም ኢትዮጵያን ከጎረቤት ሱዳን ጋር የሚያዋስን ወረዳ ነው።

በመተከል ዞን የተከሰተው የጸጥታ ችግር የጉባ ወረዳንም ሰለባ ያደረገ በመሆኑ የግድቡ ግንባታ ሂደት ላይ ስጋት ተፈጥሮ እንደነበረ የተቀናጀ ግብረ ኃይሉ ገልጿል።

የተቀናጀ ግብረ ኃይሉ ከፍተኛ አመራር አባላት በወረዳው ተገኝተው፤ የተደረገውን የአመራር ሽግሽግ በማስመልከት የስራ መመሪያ ሰጥተዋል።

የግብረ ኃይሉ ዋና ኮማንድ ፖስት አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት ጉባን መቀየር የኢትዮጵያን ሕዝብ ሕይወት መቀየር ነው።

''ጉባ ላይ የሚከፈል መስዋዕትነት ትልቅ ነው'' ያሉት ሌተናል ጄኔራሉ የጸጥታ ኃይሉ በዚህ ወረዳ ብዙ መስዋዕትነት መክፈሉን አስታውሰዋል።

አመራሩም ከጸጥታ ኃይሉ በመማር ጉባ ላይ አስተማማኝ ሰላም እንዲመጣ ጠንክሮ መስራት አለበት ብለዋል።

የወረዳው አገር ሽማግሌዎችና የውይይቱ ተሳታፊዎችም ወደ ስራ የመጡት የወረዳው አመራሮች 'ደከመኝ ሰለቸኝ' ሳይሉ ሁሉንም በአንድ አይን በማየት እንዲያገለግሉ ጠይቀዋል።

የወረዳው ሕዝብም ኢትዮጵያዊያን የሰጡት ትልቅ አደራ በመኖሩ ሕዝቡ ከአመራሩ ጋር በመሆኑ አደራውን በአግባቡ ይወጣል ብለዋል።

በቀጣይም የደፈረሰው ሰላም እንዲጠራ የሚችሉትን ሁሉ እንደሚያደርጉ ነው የገለጹት የአገር ሽማግሌዎቹ።

የጉባ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ቡሴና ረጂብ በበኩላቸው በወረዳው ያጋጠመው የጸጥታ ችግር እየተቃለለ መሆኑን ተናግረዋል።

በአካባቢው ያጋጠመው የጸጥታ ችግር የሁሉንም ኢትዮጵያዊ አንገት ያስደፋ ተግባር መሆኑን ጠቅሰው ችግሩን ሙሉ ለሙሉ ለመፍታት አመራሩ ወደ ስራ ይገባል ብለዋል።

በዞኑ ያጋጠመው የጸጥታ ችግር ከአገር አልፎ ቀጠናዊ መልክ ያለው ነው ያሉት ደግሞ የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጋሹ ዱጋዝ ናቸው።

''እንደ አገር ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቅ ችግር ነው ያጋጠመን'' ያሉት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ይህን መጥፎ ታሪክ ለመቀየር ያለው መንገድ ጠንክሮ መስራት ብቻ ነው ብለዋል።

የተቀናጀ ግብረ ኃይሉ እስካሁን በዞኑ ጉባን ጨምሮ ዳንጉር፣ ማንዱራ፣ ወምበራ፣ ቡለንና ድባጤ ወረዳዎች በመገኘት የተደረገውን የአመራር ሽግሽግ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም