በሎጂስቲክስ ችግር ምክንያት ለመርከቦች በሚሊዮን የሚቆጠር ተጨማሪ ዶላር እየተከፈለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሎጂስቲክስ ችግር ምክንያት ለመርከቦች በሚሊዮን የሚቆጠር ተጨማሪ ዶላር እየተከፈለ ነው
የካቲት 16/2013 (ኢዜአ) በሎጂስቲክስ ችግር ምክንያት ነዳጅ ለሚያመላልሱ መርከቦች በሚሊዮን የሚቆጠር ተጨማሪ ዶላር እየተከፈለ መሆኑ ተነገረ።
በነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት የሚስተዋለው የጥቁር ገበያና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴም ትልቅ ችግር ደቅኗል ተብሏል።
ነዳጅና የነዳጅ ውጤቶች አቅርቦትና ስርጭት ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በመሆን የነዳጅ ስርጭትና አቅርቦትን ፍትሃዊ ማድረግ ላይ ያተኮረ ምክክር አካሂዷል።
በምክክሩ የክልልና የፌዴራል ባለድርሻ አካላት፣ የትራንስፖርትና የፀጥታ ዘርፍ ተወካዮች ተሳትፈዋል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አህመድ ቱሳ ባቀረቡት የውይይት መነሻ ጸሁፍ የነዳጅ አቅርቦቱ ፍትሃዊ እንዳይሆን እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮችን ጠቁመዋል።
ከችግሮቹ መካከል ሎጂስቲክስ አንዱ መሆኑንና በጅቡቲ የሆራይዘን ነዳጅ ማከማቻ አቅም ዝቅተኛ መሆን ነዳጅ ሳይራገፍ መርከቦች ላይ እንዲቆይ እያደረገ እንደሆነ ገልፀዋል።
በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ እስከ 3 ሚሊዮን ዶላር እያወጣች እንደሆነና ኪሳራው ከፍተኛ በመሆኑ የማስተካከያ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት አመልክተዋል።
የነዳጅ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች እጥረት፣ ማርጀት እና ከሥራ ውጭ መሆን ሌላው የሎጂስቲክስ ችግር እንደሆነ ነው የተናገሩት።
ይህን ችግር ለማቃለል 400 ቦቴዎችን በመግዛት ወደሥራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በሌላ በኩል በነዳጅ አቅርቦት ወደ ጥቁር ገበያ የገቡ አቅራቢዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መሆኑ በጥናት እንደተደረሰበት አስታውቀዋል።
ኮንትሮባንድም ሌላው ችግር ነው ያሉት አቶ አህመድ "ነዳጅ በጅቡቲ በኩል አስገብተን በኬንያ በኩል መውጣት የለበትም፤ ከባለድርሻ አካላት ጋር የተቀናጀ ሥራ ሊሰራ ይገባል" ብለዋል።
ከጎረቤት አገራት ጋር ሲነጻጸር የኢትዮጵያ የነዳጅ ዋጋ ቅናሽ እንዳለው ገልጸው ይህም የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴው እንዲጨምር ማድረጉን አክለዋል።
የዋጋ ልዩነት መኖር ለችግሩ ምክንያት እንደሆነ ጥናቶች በማመላከታቸው በቀጣይ አንድ ዓመት የኢኮኖሚውን ነባራዊ ሁኔታ በማየት ዋጋውን የማስተካከል ሥራዎች ይሰራሉ ብለዋል።
በተለይ ከኮንትሮባንድ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት ክልሎች የጸጥታ መዋቅራቸውን በመጠቀምና የአሰራር ማሻሻያዎች በማድረግ ጠንካራ ቁጥጥር እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
የሶማሌ ክልል ጸጥታ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አብዱላሂ መሃመድ አብዲ በበኩላቸው ነዳጅ በድንበር አካባቢ ወደ ውጭ እንዳይወጣ ቁጥጥር እየተደረገ ቢሆንም የሚፈለገው ውጤት እየተገኘ አይደለም ብለዋል።
የዋጋ ቁጥጥር ክፍተት በመኖሩ ነዳጅ በሊትር እስከ 30 ብር የሚሸጥበት ቦታ አለ ያሉት አቶ አብዱላሂ ይህ ለህገወጥነት በር የሚከፍት በመሆኑ የሚመለከተው አካል መቆጣጠር ይኖርበታል ብለዋል።
ከነዳጅ አቅርቦት ጋር በተያያዘ በተለይም ቤንዚን በሚፈለገው ደረጃ እየቀረበ እንዳልሆነም አመልክተዋል።