ቀጥታ፡

18ኛው የባህል ስፖርቶች ውድድር በድሬዳዋ ይካሄዳል

የካቲት 16 ቀን 2013 (ኢዜአ) 18ኛው የባህል ስፖርቶች ውድድር ከየካቲት 21 እስከ 27 ቀን 2013 ዓ.ም በድሬዳዋ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ የባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን አስታወቀ።

ከውድድሩ ጎን ለጎን 14ኛው የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫል እንደሚካሄድ ፌዴሬሽኑ ዛሬ በሰጠው መግለጫ አመልክቷል።

የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ሰሎሞን አስፋው እንደገለጹት፤ ውድድሩ "የባህል ስፖርታችን ለአንድነታችን" በሚል መሪ ሃሳብ ይካሄዳል።

በውድድሩ ከትግራይ ክልል በስተቀር ሁሉም ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች በ11 የስፖርት ዓይነቶች ይወዳደራሉ።

ነፃ ትግል፣ የገና ጨዋታ፣ ባለ 12 እና 18 ጉድጓድ ገበጣ፣ የፈረስ ጉግስ፣ የፈረስ ሸርጥ፣ ኮርቦ፣ ለሻህ እና ለቡብ ውድድሩ ከሚካሄድባቸው የባህል ስፖርቶች ይጠቀሳሉ።

የፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በላይነህ ኃይሌ በበኩላቸው የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል መመሪያ ተዘጋጅቶ የውድድሩ ተሳታፊዎች እንዲወያዩበት መደረጉን ገልጸዋል።

ተሳታፊዎች የኮቪድ-19 ምርመራ አድርገው ውጤቱ ከተረጋገጠ በኋላ ውድድሩ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

በቤት ውስጥ የሚደረጉ ውድድሮች አካላዊ ርቀትን በጠበቀ ሁኔታ እንደሚከናወኑ ነው አቶ በላይነህ የተናገሩት።

የእርስ በርስ የልምድ ልውውጥ ለማካሄድ የሚያስችል የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫል እንደሚካሄድም ጠቁመዋል።

17ኛው የባህል ስፖርት ውድድር እና 13ኛው የባህል ፌስቲቫል ባለፈው ዓመት በአማራ ክልል ደብረ ማርቆስ ከተማ መካሄዱ ይታወሳል።የባህል ስፖርቶች ውድድር በድሬዳዋ ሲካሄድ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም