ቀጥታ፡

የኬንያ የፋይናንስ ተቋማት በኢትዮጵያ የመሰማራት ጠንካራ ፍላጎት እያሳዩ ነው ተባለ

የካቲት 16 ቀን 2013 (ኢዜአ) የኬንያ የፋይናንስ ተቋማት በኢትዮጵያ የመሰማራት ጠንካራ ፍላጎት እያሳዩ መሆኑ ተጠቆመ።

በኢትዮጵያ ከ100 በላይ የኬንያ ኩባንያዎች መዋዕለ ነዋያቸውን እያፈሰሱ እንደሚገኙም ተነግሯል።

በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የኢትዮጵያና የኬንያ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነትን የማጠናከር አላማ ያለው የበይነ መረብ የውይይት መድረክ ዛሬ ተካሄዷል።

በመድረኩ ኢትዮጵያና ኬንያ ያላቸውን የንግድና ኢንቨስትመንት አማራጮችና እድሎች አስመልክቶ ገለጻ ተደርጓል።

የኬንያ ብሔራዊ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ኤሪክ ሩቶ "ከ50 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ኬንያ ሰፊ የገበያ እድል አላት" ብለዋል።

ኬንያ በፋይናንስ፣ ቴሌኮሙኒኬሽን፣ በቴክኖሎጂና ፈጠራ፣ ትምህርት፣ አምራች ዘርፍ፣ ቱሪዝም፣ ኢነርጂ፣ ጤና እና ቱሪዝም ሳቢ የኢንቨስትመንት አማራጮችና እድሎች እንዳላት ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ለመሰማራት ፍላጎት ካላቸው የኬንያ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ የኬንያ ማዕከላዊ ባንክን ጨምሮ የተወሰኑት በባንክና በአክሲዮን ገበያ በኢትዮጵያ የግንኙነት ቢሮ መክፈታቸውን ጠቁመዋል።

"የቴሌኮም ኩባንያው ሳፋሪኮም በኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፍ መሰማራት እንደሚፈልግና ኩባንያው በሞባይል የገንዘብ ማስተላለፊያ ክፍያ ቴክኖሎጂ አገልግሎት በኢትዮጵያ የመስጠት ፍላጎት አለው" ብለዋል።

በኬንያ ብሔራዊ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት አባል የሆኑ የአነስተኛና መካከለኛ ዘርፍ የሚገኙ የንግድ ድርጅቶችና ማህበራትም ከኢትዮጵያ መንግስት ጥሪ ቢደረግላቸው የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለመመልከት ዝግጁ እንደሆኑ አስረድተዋል።

በጋራ ለመስራት እ.አ.አ በ2014 ስምምነት የተፈራረሙት የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት እና የኬንያ ብሔራዊ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት የአገሮቹ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት እንዲጠናከር እንዲሰሩ አስገንዝበዋል።

በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ ዓለም ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ መስክን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች የማሻሻያ ስራዎች ማከናወኗን ገልጸዋል።

የኢንቨስትመንት ሕጎችና አሰራሮች ላይ ማሻሻያ በማድረግ የኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ስራ መከናወኑን አምባሳደር መለስ አስረድተዋል።

"ኢትዮጵያ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝም፣ ኢንፎርሜሽንና ኮምዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ፣ ኢነርጂና ማዕድን እምቅ የሆነ የኢንቨስትመንት አማራጮችና እድሎች አሏት" ብለዋል።

በአፍሪካ ቀንድና ለመካከለኛው ምስራቅ ካላት ቅርበት አኳያ ለኢንቨስትመንትና ለንግድ ስትራቴጂካዊ የሆነ ቦታ መያዟንና ለኢንቨስተሮች ሳቢ የሆነ የማበረታቻ ማዕቀፎችን እንዳሏት ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በግልና በሽርክና ከ100 በላይ የኬንያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን እያፈሰሱ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያና ኬንያ በፖለቲካው መስክ ያላቸውን ጠንካራ ግንኙነት በንግድና ኢንቨስትመንት መስኩ ለመድገም የሚያስችል እምቅ አቅም እንዳላቸው ነው አምባሳደር መለስ ያስረዱት።

የግሉ ዘርፍ ትብብር ኢትዮጵያና ኬንያ በንግድና ኢንቨስትመንት ያላቸውን ግንኙነት ማጠናከር የሚችሉበት መስክ እንደሆነ አመልክተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጪ ንግድና ቱሪዝም ማስፋፊያ ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ረጋሳ ከፍአለ ኢትዮጵያና ኬንያ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነታቸውን ማጠናከር የሚችሉባቸውን አማራጮች መጠቀም እንደሚገባቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም